top of page

ሚያዝያ 21፣2016 - በኢትዮጵያ የዲጂታል ንግድ ሥርዓት የሚመራበት የኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው ተባለ

ይህ የተባለው የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱን ያበረታል በተባለለት የብሄራዊ ኢ-ኮሜርስ ስትራተጂ ሰነድ የግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ነው።


በመድረኩም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።


በኢትዮጵያ በተለይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ በርካት ግብይቶች በዲጅታል መንገድ በስፋት እየተከወነ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአለም አቀፍ ደረጃ በኦንላይን ግዥ የሚፈፅሙም ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኢ-ኮሜርስን በተመለከተ የህግ ማእቀፍ በበቂ ሁኔታ ያልተዘረጋ መሆኑ የግብይት እና የአሰራር ሥርዓት እንዳይበጅለት አድርጓል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቁጥትር ማእቀፍ አለመኖሩም ማህበረሰቡ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ አድርጓል ብለዋል።


የስራ እድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ ሰነድ ወደ ተግባር መግባት አስፈላጊ ነው ተብሏል።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ወይም ኢ-ኮሜርስ አንዱ መሆኑን የተናገሩት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ይህ ረቂቅ የ-ኮሜርስ ስትራቴጅ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ነው ብለዋል።


በ2024 በአለም አቀፍ ደረጃ የችርቻሮ ኢ-ኮሜርስ ሽያጭ 6.3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው የተባለ ሲሆን በ2029 18.81 ይደርሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ተብሏል።


ፋሲካ ሙሉወርቅ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: @ShegerFMRadio102_1




bottom of page