top of page

ሚያዝያ 17 2017 - የኮሪደር ልማት ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች የሚጥስ ነው የሚል ትችት፤ ከምክር ቤት አባል ቀረበበት

  • sheger1021fm
  • Apr 25
  • 2 min read

እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት ''ዜጎችን ከአካባቢያቸው ያፈናቀለ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የሚጥስ ነው'' የሚል ትችት፤ ከምክር ቤት አባል ቀረበበት፡፡


መንግስት በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እና ፍትሃዊነት ያረጋገጠ ነው ብሏል፡፡


ትችቱ የቀረበው የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የ9 ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡


የምክር ቤት አባሉ አበባው ደስአለው(ዶ/ር) የኮሪደር ልማቱ ከሰብአዊ ተቋማትም፣ ከሚዲያዎችም፣ ከማህበረሰቡም፣ ቅሬታ እየቀረበበት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡


ለማሳያም ባለፈው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡


የምክር ቤት አባሉ የኮሪደር ልማቱ ሲተገበር የሰብአዊ መብቶች መጣሳቸውን ሪፖርቶች እንደሚሳዩ ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡


ለማሳያም ከልማት ተነሺዎች ጋር በቂ ምክክር አልተደረገም፣ ለተነሺዎችም በቂ ካሣ እና ምትክ አልተሰጣቸውም፣ ተነሺዎቹ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉም አስቀድሞ የፅሁፍ ማስጠንቀቅያ እንዳልተሰጣቸው ሪፖርቱን ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡


ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር መወከላቸውን የተናገሩ አቡኔ አለም የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፤ ከማህበረሰቡ እና ከሰብአዊ ተቋማት በኮሪደር ልማቱ ላይ ቅሬታ እየቀረበ ነው የሚለውን ሃሳብ እንደማይቀበሉ ተናግረው፤ እንዲያውም ማህበረሰቡ እየጠየቀ ያለው መቼ ነው ሁሉም ጋር የሚደርሰው? የሚለውን ነው ብለዋል፡፡


ለማ ተሰማ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው በተለያዩ ክልሎች፤ በተለይ በአዲስ አበባ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት የሀገሪቱን ገጽታ የቀየረ፣ ዜጎችንም ያኮራ ነው ብለዋል፡፡


አቶ ለማ በማከልም አንዳንድ ወገኖች ልክ የካሣ ክፍያ እንዳልተከፈለ፤ እንደዚህም ቤታቸው ለፈረሰባቸው ሌላ መጠለያ እንዳልቀረበላቸው እየተደረገ የሚነሳ ነገር አለ ይህ ሁኔታ እንዴት ባለ መልኩ ነው መልስ እያገኘ ያለው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


ለጥያቄዎቹ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢ/ር ጫልቱ ሳኒ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች በኮሪደር ልማት ታሪካዊ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡


ይህን ማድነቅ የማይችል ኢትዮጵያዊ ካለ እውነት ኢትዮጵያን ይወዳታል ወይስ አይወዳትም የሚለውን መጠየቅ ያሻል ብለዋል፡፡


ስለ ሰብአዊ መብት የሚጨነቁ ተቋማት የእኛ ዜጎች በፕላስቲክ ሲፀዳዱ፣ በቆጥ ሲኖሩ፣ ክብረ ነክ የሆነ መኖሪያ እና ሰፈር ላይ ሲኖሩ ምነው መብታቸው ተነካ አላሉም? ሲሉ ጠይቀው ዛሬ ላይ እኮ የትኛውም መንግስት በየትኛውም አገር በየትኛውም ደረጃ ተይቶ የማይታወቅ ታሪካዊ ስራ ነው በከተሞቻችን እየተሰራ ያለው ብለዋል፡፡


የካሣ እና ምትክ ቦታን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም ሚኒስትሯ በምላሻቸው፤ ከተሞቻችን ላይ ለኮሪደር ልማት የፈረሱ ቤቶች 90 በመቶ የሚሆነው የመንግስት የኪራይ ቤቶች መሆናቸው ጠቅሰው 11,572 ቤቶች ናቸው በዝቅተኛ ኪራይ ወይንም በነፃ በሚባል ደረጃ ለዜጎቻችን የቀረበው ሲሉ መልሰዋል፡፡


የኮሪደር ልማቱ ሰው ተኮር ነው ያሉት ሚኒስትሯ ፍታዊ እና የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/gdf/



ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page