ሚያዝያ 17 2017 - ኢትዮ ቴሌኮም የካፒታል ገበያ ወደ ኢኮኖሚው መግባቱን ተከትሎ በመጀመርያው ዙር የህዝብ አክስዮን ሽያጭ ከተሳተፉ ኢንቨስተሮች መካከል ምንም የምሰርዘው ደንበኛ የለም አለ
- sheger1021fm
- Apr 25
- 2 min read
ኢትዮ ቴሌኮም የካፒታል ገበያ ወደ ኢኮኖሚው መግባቱን ተከትሎ በመጀመርያው ዙር የህዝብ አክስዮን ሽያጭ ከተሳተፉ ኢንቨስተሮች መካከል ምንም የምሰርዘው ደንበኛ የለም አለ።
ኩባንያው ይህን የተናገረው ዛሬ 47,300 ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበትን ገበያ ሽያጭ በተናገረበት ወቅት ነው።
ይህ ገበያ ለሐገር ውስጥ ደንበኛ ብቻ የቀረበ እንዲሁም በአነስተኛ ዋጋ ሁሉንም ለማሳተፍ የታሰበ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ይህ ገበያም አዲስ እንደመሆኑ መጠን የዲጂታል ማህበረሰብን ፈጥረንበታል ወደፊት ለሚደረገው የኢኮኖሚ ጉዞ መንገዱን አይተንበታል ብለዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ ውጤት በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አካላት ተገምግሞ እንዲሁም በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (Ethiopian Capital Market Authority) ታይቶ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ተወስኗል ተብሏል።
በአክሲዮን ሽያጩ ወቅት ብዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ተቋማት እና ውጪ የሚኖሩ ባለሀብቶች ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል ተብሏል።

ቢሆንም ግን በቅድሚያ በሀገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ በዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ ሲከናወን ቆይቷል ተብሏል።
ግዙፋ ኢትዮ ቴሌኮም ለድርሻ ገበያ የቀረበው ደንበኞች በመተማመን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ወደፊትም አክሲዮናቸውን ማንቀሳቀስ ወደ ሚችሉበት የሰነደ መዋዕለ ንዋይ (Stock Market) ልምምድ በመግባት በኢኮኖሚው እንዲካተቱ የታሰበ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች በስፋት በመሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይከ47,377 ዜጎች ከ10.7 ሚሊዮን የኢትዮ ቴሌኮም መደበኛ አክሲዮኖች የግዢ በዲጂታል መንገድ በማከናወን ብር 3.2 ቢሊየን የሚጠጋ ሀብት ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡
ወደፊት ከእያንዳንዱ አመልካች ጋር በሚኖር የቀጥታ ግንኙነት ያልተሟሉ መረጃዎችን የማሟላት ተግባር በማከናወን የተቋሙ ባለቤት የሚሆኑበት ማረጋገጫ የመስጠት ስራ ይከናወናል ተብሏል።
ኩባንያው የተሸጡ አክሲዮኖች ድልድል በካፒታል ገበያ ባለስልጣን የማጽደቅ ሂደት ከተከናወነ በኋላ ውጤቱን በይፋ እናሳውቃለን ብሏል።
የተደለደሉ አክሲዮኖች በማዕከላዊ የሰነዶች ሙዓለ ነዋዮች ግምጃ ቤት ከተመዘገቡና ይህም ሂደት እስኪጠናቀቅ ኩባንያው መረጃዎችን
ለባለአክሲዮኖች ደረጃ በደረጃ እሰጣለሁ ብሏል፡፡
የኩባንያው ባለድርሻ የሚሆኑ ባለአክስዮኖች ወደፊት በኢትዮጵያ የሰነዶች ሙዓለ ነዋዮች ገበያ አክስዮናቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ በገበያው እንዲመዘገብ የቤት ስራዎች ይከናወናሉ ተብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም ቀሪ አክስዮኖች በተመለከተም ዝርዝር የሽያጭ ሂደቱን አሳውቃለሁ ያለ ሲሆን፤ አሁን አክሲዮን የገዙ ባለድርሻዎችን መብት ባስጠበቀ መልኩ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ይሁንታ በማግኘት በድጋሚ ለገበያ የሚቀርቡ መሆኑን አስረድቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም የ30 ቢሊየን ብር ወይም የ 10 በመቶ ድርሻውን አክሰዮን ለህዝብ ሽያጭ ክፍት ያደረገው ጥቅምት 7 2017 ዓ.ም ነበር።
ኢትዮ ቴሌኮም በመጀመርያው ምእራፍ በመደበኛ የአክስዮን ሽያጭ 100 ሚሊየን ሼር ለደንበኞቹ ለመሸጥ ወደ ገበያ አውጥቶ ነበር።
ይህ 100 ሚሊየን ሼር በገንዘብ ሲሰላ 30 ቢሊየን ብር እንደሚተመን ከደንበኛ ሳቢ መግለጫው ላይ አንብበናል።
ለካፒታል ገበያ መንገድ የከፈተውና የመጀመርያ የመደበኛ የኢትዮ ቴሌኮምን የ 10 በመቶ ሽያጭ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments