top of page

ሚያዝያ 1 2017 - ታሪክን የኋሊት - ባግዳድ የየተያዘችበት ቀን

  • sheger1021fm
  • Apr 9
  • 2 min read

በአሜሪካና በተባባሪዎቿ ወረራ ፣ኢራቅ፣ ተሸንፎ ባግዳድ የተያዘችው ፣ በ1985 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡


አሜሪካና አጋሮቿ ባግዳድን ተቆጣጥረው፣ ለሳዳም ሁሴን መንግስት እንደምልክት የሚታየውን ፣ የሳዳምን የነሐስ ሐውልት ፣ ለማፍረስ የቻሉት ፣ ከሶስት ሳምንታት ውጊያ በኋላ ነው፡፡


አሜሪካና እንግሊዝ ቀዳሚ ሆነው፣ የሚመስሏቸውን ሃገሮች አስተባብረው ፣ የሳዳም ሁሴንን መንግስት የዘመቱበት ፣ ኢራቅ ሕዝብ ጨራሽ የኬሚካል መሳሪያ ታጥቃለች የሚል ምክንያት ሰጥተው ነው፡፡

ree

የኬሚካል መሳሪያው ስለመኖር አለመኖሩ በተመድ ስር ያለው የአለም አቶሚክ ኤጀንሲ እንዲመረመር ታዘዘ፡፡


ሳዳም፣ በፊት እምቢ ቢሉም፣ በኋላ ፈቃደኛነታቸውን ገልፀው ነበር፡፡

ያን ጊዜ፣ አሜሪካና አጋሮቿ ጦራቸውን ወደ ኢራቅ ድንበር አስጠግተው ስለነበር ለመነጋገር ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡


ለተልኳቸውም ፣የኢራቅን ህዝብ ነፃ ለማውጣት፣ ሳዳም ሁሴን ለአሸባሪዎች ደጋፊነታቸውን ለማቋረጥ፣ የሚል ምክንያት ጨመሩበት፡፡


አሜሪካ ፣ እንግሊዝ ፣ ፖላንድና አውስትራሊያ 160 ሺህ ወታደሮች ሲልኩ ሌሎች 36 ሃገሮች ለዘመቻው የተለያየ ድጋፍ አድርገዋል፡፡


የዘመቻው ምክንያት በተመድ ስላልተደገፈ አሜሪካ የማስተባበር ሀላፊነቱን ወስዳ ዘመቻው ተጀመረ፡፡


ከሶስት ሳምንት ጦርነት በኋላ ባግዳድን እነ አሜሪካ ተቆጣጠሩ፡፡

ሳዳም ሁሴን አምልጠው ተደበቁ፡፡


ፕሬዘዳንት ጆርጅ ቡሽ የጦርነቱ የመጀመሪያው እቅድ ተጠናቀቀ አሉ፡፡

ግን ባግዳድ ብትያዝም ጦርነቱ በየቦታው ተቀሰቀሰ፡፡


ሸማቂዎች በኢራቅ ግዛቶች ተሰራጭተው የአሜሪካን ወታደሮች ጭምር አጠቁ፡፡

ሳዳም ሁሴንን ፈልጎ ለማግኘት እንኳ 11 ወር ፈጅቷል፡፡


አሜሪካና ተባባሪዎቿ የመንግስት ሀላፊዎች የነበሩትን ሲያሳድዱ ቆዩ፡፡

የሳዳም ሁለት ልጆችም ተገደሉ፡፡


ሳዳም ሁሴን ከተያዙ ሶስት አመት በኋላ፣ በሞት እንዲቀጡ ስለተፈረደባቸው ተሰቀሉ፡፡

ይኽም ሁሉ ሆኖ ጦርነቱ አልተቋጨም፡፡


አሜሪካ በይፋ ወታደሮቿን ያስወጣችው ከስምንት አመት በኋላ ሲሆን በነዚያም አመታት ከ4 ሺህ በላይ ወታደሮቿ በኢራቅ አማፅያን ተገድለዋል፡፡


ኢራቅ አዲስ አስተዳደር መሰረተ፡፡

ግን ኢራቅ ታጥቃዋለች የተባለው ህዝበ ጨራሽ የኬሚካል መሳሪያ አልተገኘም፡፡


አሜሪካ የሰጠችው ሀሰተኛ መረጃ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች አልቀዋል፡፡

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሊር በኋላ መፀፀታቸውን ሲናገሩ ፕሬዘዳንት ቡሽም የመረጃ ስህተት መኖሩን አምነው ፣ ሀላፊነቱን እወስዳለሁ አሉ፡፡


አሜሪካ በወረራ ባግዳድን ከተቆጣጠረች 22 ዓመት ሞላ፡፡


እሸቴ አሰፋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page