top of page

መጋቢት 28፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች



አዲሱ የሴኔጋል ፕሬዘዳንት ባሲሩ ፌይ 25 ሚኒስትሮችን ሾሙ፡፡


ቀደም ሲል ፕሬዘዳንቱ የፖለቲካ እውቀት ኮትኳቻቸው የሆኑትን ኦስማኔ ሶንኮን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሰየማቸውን TRT አፍሪካ አስታውሷል፡፡


በሴኔጋል በሚኒስትርነት የተሾሙት ለመንግስታዊ ሀላፊነቱ አዳዲሶች ናቸው ተብሏል፡፡


ከመካከላቸውም አራቱ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡


ባሲሩ ፌይ ወደ ቤተ መንግስት የገቡት ከእስር በተፈቱ በ10ኛው ቀን በተካሄደው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ አሸንፈው ነው፡፡


ፕሬዘዳንቱ የ25 ሚኒስትሮችን ሹመት ያፀደቁት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት መሆኑ ታውቋል፡፡



የሊባኖሱ የጦር ድርጅት (ሔዝቦላህ) መሪ ሐሰን ናስረላህ እስካሁን ጥቅም ላይ ያላዋልናቸው አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን አሉን ማለታቸው ተሰማ፡፡


ናስረላህ አዳዲስ መሳሪያዎች አሉን ማለታቸው የተሰማው እስራኤልን ባስጠነቀቁበት ንግግራቸው እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፋል፡፡

የሔዝቦላህ መሪ ማስጠንቀቂያ የተሰማው ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዷ አይቀርም የሚለው ግምት ባየለበት ወቅት ነው፡፡


ናስረላህም ምን አለ በሉኝ ይሄ አይቀሬ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ሔዝቦላህ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ አጋር መሆኑ ይነገራል፡፡


በሶሪያ ርዕሰ ከተማ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ፅህፈት ቤት ላይ በተፈፀመ ድብደባ ሁለት ጄኔራሎችን ጨምሮ 7 የኢራን የጦር መኮንኖች መገደላቸው ኢራንን ቱግ አድርጓታል፡፡


ለድብደባው እስራኤልን በተጠያቂነት የከሰሱት የኢራን መሪዎች እስራኤል የእጇን ታገኛለች እያሉ ነው፡፡



የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የፕሬዘዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለእስራኤል የጦር መሳሪያ መሸጡን እንዲያስቆም ጠየቁ፡፡


ፔሎሲ እና ሌሎችም የዲሞክራቲክ ፓርቲው እንደራሴዎች ፊርማቸውን ያኖሩበት ደብዳቤ ለፕሬዘዳንት ባይደን እና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መላኩን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


የቀድሞዋ የህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በፕሬዘዳንቱ የፖለቲካ አጋርነት ይታወቃሉ፡፡


እስራኤል በጋዛ ዘመቻዋ በሰላማዊ ፍልስጤማውያን ላይ እልቂት እያደረሰች ነው የሚል ውግዘት እየደረሰባት ነው፡፡


በዚሁ ጉዳይ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ በማቅረብ አሜሪካም ከወቀሳው አላመለጠችም፡፡


አሁን ደግሞ ባይደን ለእስራኤል የጦር መሳሪያ እንዳያቀርቡ በቅርቦቻቸው እስከመጎትጎት ደርሰዋል ተብሏል፡፡



ሰሜን ኮሪያ በርካታ ክሩዝ ሚሳየሎችን መተኮሷ ተሰማ፡፡


የደቡብ ኮሪያ የጦር ሹሞች ሰሜን ኮሪያ በርካታ የክሩዝ ሚሳየሎችን መተኮሷን አረጋግጠናል እንዳሉ አሜሪካን ሚሊታሪ ኒውስ ድረ ገፅ ፅፏል፡፡


ደቡብ ኮሪያ ከነአሜሪካ ጋር በጣምራ የጦር ልምምድ ላይ ሰንብታለች፡፡


ሰሜን ኮሪያ የእነ አሜሪካ የጦር ልምምድ እንደ ከፍተኛ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቷ ትቆጥረዋለች፡፡


ሰሜን ኮሪያ ካለፈው ጥር ወር ወዲህ የታላላቅ የጦር መሳሪያዎች ሙከራዋን ድግግሞሽ እየጨመረች ነው ይባላል፡፡


ሁለቱ ኮሪያዎች ከ70 አመታት በፊት ታላቅ ጦርነት ካደረጉ ወዲህ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት ተለይቶት አያውቅም፡፡


የኔነህ ከበደ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





ShegerFM: @ShegerFMRadio102_1

bottom of page