top of page

መጋቢት 19፣2016 - ለ64 ሆቴሎች በተደረገ የሆቴሎች ምዘና ባለ 5 ኮኮብ ደረጃ ያሟላ የለም ተባለ

በ2014 እና በ2015 ለ64 ሆቴሎች በተደረገ የሆቴሎች የደረጃ ምዘና ባለ 5 ኮኮብ ደረጃ ያሟላ የለም ተባለ።


የቱሪዝም ሚኒስቴር በወቅቱ ለ 64 ሆቴሎች ምዘና አድርጎ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ አሟልተው ለተገኙ 31 ሆቴሎች ደረጃ የመደበ ሲሆን አንድም ሆቴል የባለ 5 ኮከብነት ደረጃ ያሟላ ሆቴል አልተገኘም ተብሏል።


የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ እንዳሉት አዲስ አበባን ጨምሮ በሀዋሳ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሻሸመኔ፣ ዱከም ምዘናው ተካሂዶ መስፈርቱን ያሟሉት 31 ሆቴሎች ደረጃ ተሰጥቷቸዋል።


7 ሆቴሎች ባለ 4 ኮከብ ደረጃ፣ 9 ሆቴሎች ባለ ሶስት ኮከብ፣ 5 ሆቴሎች ባለ 2 ኮከብ ደረጃ፣ 8 ሆቴሎች ባለ 1 ኮከብ ደረጃ ሲያገኙ ቀሪ 2 ሆቴሎች ከደረጃ በታች ናቸው ተብሏል።



በ2007 በተደረገ የደረጃ ምደባ 365 ሆቴሎች ተመዝነው የነበረ ሲሆን በ2011 ደግሞ 91 ሆቴሎች የደረጃ ምዘና ተደርጎላቸው እንደነበር ሰምተናል።


ከእነዚህ ውስጥ 340 ቱ ከደረጃ 1 እስከ 5 ድረስ ተመድበው ነበር ያለው የቱሪዝም ሚንስቴር በኮቪድና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ከ2011 በኋላ የደረጃ ምዘና አለማድረጉን ተናግሯል።


የሆቴሎች ድረጃ በየ 2 አመት መካሄድ አለበት የተባለ ሲሆን ይህም በአለማቀፍ ደረጃ ቱሪዝሙ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያደርጋል ሲሉ ሚንስትሯ ተናግረዋል።


ከመጪው ሳምንት ጀምሮ በሆቴሎች ዳግም የደረጃ ምዘና ይደርጋል ለዚህም ሆቴሎች ዝግጅት እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል ተብሏል።


የአስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሎጆች ወደፊት የደረጃ ምዘና እንደሚደረግላቸው ሰምተናል።


በረከት አካሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




bottom of page