መስከረም 9 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Sep 19
- 2 min read
የእስራኤሉ የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በጋዛ ሰርጥ ባለ ከፍተኛ ሐብት የሪል ስቴት ግንባታዎችን እንገጠግጥበታለን አሉ፡፡
ሰርጡ በእስራኤል እና በአሜሪካ ይዞታነት እንደሚካፈልም ስሞትሪች መናገራቸውን CNN ፅፏል፡፡
ስሞትሪች አሜሪካውያንም በጋዛው ዘመቻችን ገንዘባቸውን ስለከሰከሱ ከጋዛ ሰርጥ ድርሻቸውን ያገኛሉ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የእስራኤሉ የገንዘብ ሚኒስትር የጋዛው ውጥናችን የአዋጭነት ጥናት ለአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀርቦላቸዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ትራምፕ ቀደም ሲል የጋዛ ፍልስጤማውያንን በአቅራቢያው አገሮች በማስፈር ሰርጡን ወደ ቱሪስቶች መዝናኛ መናኸሪያነት እቀይረዋለሁ ካሉ ቆይተዋል፡፡
የእነ ትራምፕ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ሰርጥ የመንቀል ውጥን ከየአቅጣጫው ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው የአፍጋኒስታኑን የባግራም የአየር ሀይል ሰፈር መልሳ ለመያዝ መሞከሯ አይቀርም አሉ፡፡
የአፍጋኒስታኑን አየር ሀይል ሰፈር መልሳ በእጇ ለማስገባት አሜሪካ ከታሊባን አስተዳደር ጋር ሚስጠራዊ ድርድር ስታካሂድ መቆየቷን ትራምፕ መጠቆማቸውን TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡
አሜሪካ በተዘበራረቀ ሁኔታ የባግራምን የአየር ሀይል ሰፈር ለቅቃ የወጣችው ከ4 አመታት በፊት ነው፡፡
እንደሚባለው ትራምፕ ይህን የአየር ሀይል ሰፈር መልሳ በእጇ ለማስገባት ያለሙት ቻይናን በቅርበት ለመከታተል ብለው ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ትራምፕ የአሜሪካ ጦር ባግራምን ለቅቆ መውጣቱን በቁጭት እያነሱት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ባግራምን በእጅጉ ያስፈልገናል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ካምቻትካ የባህር ዳርቻ ከባድ ነውጥ ደረሰ፡፡
በካምቻትካ የባህር ዳርቻ የደረሰው ከባድ ነውጥ በርዕደ መሬት መለኪያ /ሬክተር ስኬል/ 7 ነጥብ 8 ሆኖ መመዝገቡን AFP ፅፏል፡፡
ከዋናው ነውጥ በተጨማሪ 5 ያህል መለስተኛ መንቀጥቀጦችም አጋጥመዋል ተብሏል፡፡
በነውጡ በሰዎች ላይ ስለደረሰ አንዳች ጉዳት የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ቀጠናውን ከባድ የመሬት ነውጥ እየደጋገመው ነው፡፡
በሐምሌ ወርም የባህር ዳርቻው በርዕደ መሬት መለኪያ /ሬክተርስ ስኬል/ 8 ነጥብ 8 የሆነ ከባድ ነውጥ አጋጥሞት እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
ከአሁኑ ነውጥ በኋላ ከፍተኛ የባህር ማዕበል /ሱናሚ/ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ታውቋል፡፡
የማላዊ የምርጫ ኮሚሽን የፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ተፎካካሪዎች በራሳቸው አሸናፊነታቸውን ከማወጅ እንዲቆጠቡ አስጠነቀቃቸው፡፡
ማላዊያን መጪውን ፕሬዘዳታቸውን እና የፓርላማ እንደራሴዎቻቸውን ለመምረጥ ማክሰኞ እለት ድምፅ መስጠታቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ከፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ተፎካካሪዎች መካከል የአሁኑ ፕሬዘዳንት ላዛረስ ቻክዌራ እና ቀዳሚያቸው ፒተር ሙታሪካ በየፊናቸው በምርጫው አሸንፈናል እያሉ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ ግን ከእኔ በስተቀር የትኛውም ተፎካካሪ በራሱ አሸናፊነቱን የማወጅ መብት የለውም ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ተፎካካሪዎቹም ሆኑ መራጮች የኮሚሽኑን ይፋዊ ውጤት መጠበቅ ይኖርባቸዋል ብሏል ኮሚሽኑ፡፡
ማላዊያን የማክሰኞውን የምርጫ ውጤት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments