መስከረም 6 2018 - በመሬት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን እና የፍርድ ቤት ክርክሮችን ለመቀነስ የመሬት ምዝገባ ዋነኛው መፍትሄ ነው ተባለ
- sheger1021fm
- Sep 16
- 1 min read
በመሬት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን እና የፍርድ ቤት ክርክሮችን ለመቀነስ የመሬት ምዝገባ ዋነኛው መፍትሄ ነው ተባለ።
ይህ የተባለው በጀርመን ትብብር ድርጅት(giz) አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለ የመሬት አስተዳደር ስልጠና ላይ ነው።
በስልጠናው እና ልምድ ልውውጡ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ልማት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዳይሬክተር ትዕግስቱ ገ/መስቀል መሬትን መዝግቦ ማስተዳደር ካልተቻለ መሬት የልማት እና የሃብት ምንጭ መሆን ቀርቶ የግጭት እና የክርክር ምክንያት ይሆናል ብለዋል።

እያንዳንዱ አባወራ መሬቱ የት እንደሚገኝ፣ ምን ያህል እንደሆነ እና ከማን ጋር እንደሚዋሰን በባህላዊ መንገድ አውቋል ያሉት ዳይክተሩ ግን ያ መረጃ ለተንታኞች እና ለፖሊሲ አይመችም ብለዋል።
ለዚህም እንዲረዳ የግብርና ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ ሰርተፍኬት መሰጠት መጀመሩ ተነግሯል።
በገጠር ያሉ የአርሶ አደር መሬቶች የተበጣጠሱ፣ ለልማት እና ለአስተዳደር አመቺ አይደሉም ብለዋል በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ልማት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዳይሬክተር ትግስቱ ገ/መስቀል።
እነዚህን መሬቶች በዘመናዊ መንገድ መዝግቦ ወደ ስረዓት ማስገባት ያስፈልጋል ያን ማድረግ ከተቻለ በቤተሰብ እና በጎረቤት መካከል በወሰን የሚፈጠሩ ግጭቶች ቀንሶ መሬትን ለልማት ማዋል ይቻላል ተብሏል።
ዛሬ በተጀመረው ስልጠና ላይ ከቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቫር፣ ማዳጋስካር፣ ኒጄር፣ ኡጋንዳ የመጡ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን ለሶስት ቀናት ስልጠናው እንደሚቆይ ተነግሯል።
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments