መስከረም 29 2018 - የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር በጅቡቲ የነፃ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታ (ፍሪ-ዞን) አገልግሎት ለማግኘት በመንገድ ላይ መሆኑ ተሰማ።
- sheger1021fm
- Oct 9
- 2 min read
የባቡር መስመርን በራስ አቅም፤ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ከነፃ የንግድ ቀጠናዎች፣ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ዞኖችን እና ከሎጂስቲክስ ማዕከላት ጋር ለማስተሳሰር የሚደረገው ጉዞ በይፋ መጀመሩ ተነግሯል።
ይህን ያሉት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ናቸው።
ከኢትዮዽያ የገቢና ወጪ ንግድ ጋር በተገናኘ በተለይ በሎጅስቲክስ ምዕራፍ የትራንስፖርት መስመሩ አሁንም ከፍተኛ ወጪ እና እንግልት ያለበት መሆኑና ይህንንም ለማስቀረት መንገድ መጀመሩ ሲነገር ሰምተናል።
ከ90 በመቶ በላይ የሀገሪቱ ገቢና ወጪ በምስራቅ የኢትዮዽያ ክፍል የሚተላለፍ በመሆኑ፤ በዚህ መስመር የሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፣ ወጪና ገቢ እቃዎችን በተሻለ የሎጅስቲክስና የባቡር መስመር እንዲያቀላጥፉ መታቀዱ ተነግሯል።
በዚህም መሰረት እነዚህን ኢንዱስትሪዎች ከኢት-ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር በማገናኘት የሎጂስቲክስ መደነቃቀፉን ለማሻሻል እንዲያግዝ ስራ መጀመሩን የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ተናግሯል።
ይህን ተከትሎ ዛሬ የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ኤ.ኤም.ጂ ኢንደስትሪያል ፓርክን ከእንዶዴ የባቡር ጣቢያ ጋር የሚያገናኝ የ3ኪ.ሜ የባቡር መስመር ግንባታ መጀመሩ ተነግሯል።
በዚህም ቡናና ብረታ ብረቶችን ጨምሮ የኤ.ኤም.ጂ ምርቶችን ከበር ወደ ወደብ በፍጥነት ማጓጓዝ የስችላል።
ይህ የሚነጠፈው የባቡር መሰረተ ልማት ሙሉ በሙሉ፤ ለመጀመርሪያ ጊዜ በኢትዮጵያዊያን የባቡር ምህንድስና ባለሞያዎች አቅም የሚገነባ መሆኑ ታውቋል።
ፕሮጀክቱ እንዶዴ የባቡር ጭነት ጣቢያን ከኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር በማስተሳሰር የተሻለ እና ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመሰጠት እንደሚያግዝ ሰምተናል።
የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈፃሚ ታከለ ኡማ፤ የኢትዮዽያን የባቡር መሰረተ ልማት መገንባት፤ አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በብርቱ ያሻሽላል ካሉ በኋላ የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ከአንድ ኩባንያ አልፎ ወደ ተለያዩ ኩባንያዎች ስብስብ ወይም ሆልዲንግስ ይሸጋገራል ብለዋል።

ምድር ባቡሩ በሶስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማለትም የከፍተኛ ሀይዌይ የባቡር ንጣፍ መዘርጋት፤ ጅቡቲ ከመድረስ ባለፈ የሀገሪቱን ገቢ ወጪ እቃ ወደ ተቀረው አለም ዘርግቶ የግሎባል ሎጅስቲክስ ጉዞ ማቀላጠፍ እና የባቡር ኦፕሬሽን ጥገና እና ምህንድስና ላይ ለመስራት ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል።
ዛሬ የተጀመረው የባቡር ሀዲድ ማገናኘት ፕሮግራም ከሀገር ቤት ባለፈ የጎረቤት ሀገራትን ጭምር በባቡር ለማስተሳሰር ሀሳብ እንዳለ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ተናግረዋል።
የባቡር መሰረተ ልማት በሁሉም አቅጣጫ ተሳስሮ የአፍሪካን አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ለማሳካት በብርቱ መስራት እንደሚያስፈልግና እንደሚደግፍ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እንደዛሬው አይነት የባቡር መንገድ ንጣፍ ፤ ጥሬ ዕቃዎችን ከወደብ ወደ ፋብሪካው እንዲሁም ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ሸቀጦችን ወደ ወደብ በማድረስ በየመንገዱ ያለውን የተዝረከረከ የሎጅስቲክስ አሰራር ያስቀራል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የባቡር መሠረተ ልማት ታሪክ ሁሉንም ተግባራት በኢትዮጵያዊያን ባለሞያዎች እንዲከናወኑ በማድረግ መንገድ ያሳየ መሆኑንም ሰምተናል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx












Comments