መስከረም 27 2018 - ቴሌ የሰራውን መብራት ሃይል ያፈርሳል ፤ የመንገዶች አስተዳደር የገነባውን ውሃና ፍሳሽ ይንደዋል እያሉ ብዙ ሰዎች ያማርራሉ
- sheger1021fm
- Oct 7
- 2 min read
ቴሌ የሰራውን፣ መብራት ሃይል አፈረሰው ፤ መንገዶች ባለስልጣን የገነባውን ውሃ እና ፍሳሽ አነሳው የሚሉ የቅሬታ አስተያየቶች በተለያየ ጊዜ ይሰማሉ።
ተቋማቱ መሰረተ ልማት ሲዘረጉ ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያስተባብር ኤጀንሲም ተቋቁሞ ነበር።
በኋላ ላይ ደግሞ ተቋማቱን የማስተባበሩ ስራ ለከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ተሰጥቷል። ታዲያ ምን ለውጥ መጥቶ ይሆን ?
መሰረተ ልማት በሚዘረጉ ተቋማት መካከል የመናበብ ችግር እንዳለ ተደጋግሞ ይነገራል።
በተቋማቱ መካከል ለምን ቅንጅት እንደማይኖርም አብረው ይጠይቃሉ።
ቅሬታው በተቋማቱም የሚታወቅ ነው። ተቀናጅተን ለመስራት ተስማምተናል የሚል መግለጫ በተለያየ ጊዜ ሲሰጡ መሰደመጣቸውም ይህንኑ ያሳያል።
በተግባር ግን ብዙም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ነው ከህብረተሰቡ የሚሰማው።
ተቀናጅተው እንዲሰሩ የማስተባበሩን ሃላፊነት እንዲወጣ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ኤጀንሲ የሚባል ድርጅትም ተቋቁሞም ነበር።
2014 ላይ ግን ይህ ድርጅት ፈርሶ ተቋማቱን የማስተባበሩን ስራ ለከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ተሰጥቷል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በመሪ ስራ አስፈጻሚ የሚመራ አንድ ክፍል አቋቁሞ ስራውን ሲሰራ ቆይቷል።
ተቋማቱ መሰረተ ልማት ሲዘረጉ በቅንጅት ሰርተዋል አልሰሩም የሚለውን እያጣራ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት የማቅረብ ሃላፊነትም ታክሎለታል።
ለመሆኑ ስራው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተሰጠ በኋላ ነገሮች ምን ያህል ተሻሽለዋል ስንል ጠይቀናል።
ስራው መሰረተ ልማቶቹን የሚዘረጉ ተቋማት በጋራ አቅደው እንዲሰሩ ከማድረግ ስራው እንደጀመረ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ኢትዮጵያ በዴቻ ነግረውናል።
መሰረተ ልማቶችን በሚዘረጉ ተቋማት መካከል መናበብ የለም የሚለው የህብረተሰቡ ቅሬታ አሁን ላይ ቀንሷል ያሉት ስራ አስፈጻሚው የአዲስ አበባ ሁኔታ የዚህ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን ላይ አንዱ ተቋም የሰራሁትን መሰረተ ልማት አበላሸብኝ ብሎ ሲከስ ብዙም እንደማይሰማ ዋና ስራ አስኪያጁ ነግረውናል።
ይሄ ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪም ባሉ አካባቢዎች ያለ እውነታ ነው ነው ብለዋል።
የተቋማቱ ተናቦ አለመስራት ከፍተኛ የሆነ የሃብት ብክነት እንዲከሰት ሲያደርግም ቆይቷል የሚሉት አቶ ኢትዮጵያ፤ የማቀናጀቱ ስራ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተላለፈ በኋላ ይህም መቀነሱን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ስራው በሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ይህንኑ የተቋማቱን ቅንጅት የተመለከተ ሃሳብም እንደሚያካትትም ሠምተናል።
አሰራሩ እየታየ ተጨማሪ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም አቶ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
በእስከ አሁን ቆይታው ስላከናወናቸው ተግባራት የጠየቅናቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ኢትዮጵያ በዴቻ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ግን ይህንኑ ችግር የሚያስቀር አንድ ተቋም እንደተደራጀ ተነግሮ ነበር።
ተቋሙ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶችን የማቀናጀት ሃላፊነት እንደተሰጠው ነው የተነገረው።
ተቋማቱ መሰረተ ልማት ሲዘረጉ በቅንጅት ሰርተዋል አልሰሩም የሚለውን እያጣራ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፤ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ሌሎች መስሪያ ቤቶች ሪፖርት ያቀርባልም ተብሎ ነበር።
በእስከ አሁን ቆይታው ስላከናወናቸው ተግባራት የጠየቅናቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ኢትዮጵያ በዴቻ ተናግረዋል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx












Comments