መስከረም 14 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Sep 24
- 1 min read

ጀርመን የወታደሮቿን ብዛት እና የመከላከያ ወጪዋን በእጅጉ ልትጨምር ነው ተባለ፡፡
አገሪቱ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ለመመልመል መሰናዳቷን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀርመን የጦር አቅም ማደርጃ ውጥን ደጋግሞ እየተሰማ ነው፡፡
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት /ኔቶ/ አባል አገሮቹ የጦር ወጪያቸውን እንዲያሳድጉ ቀደም ሲል ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡
የጀርመንም የሰራዊት አባላት ማብዛት እና የጦር አቅምን ማደርጀት የዚሁ ውሳኔ አካል ነው ተብሏል፡፡
ኔቶ በአሁኑ ወቅት ከሩሲያ ጋር በቋሚ የጦር ፍጥጫ ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡

በሱዳን የኮሌራ ወረርሽኙ እየተባባሰ ነው ተባለ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በሱዳን የኮሌራ ወረርሽኝ መዛመት በእጅጉ ከአሳሳቢው ደረጃ ላይ ደርሷል ማለቱን አናዶሉ ፅፏል፡፡
ወረርሽኙ ከአመት በፊት አንስቶ በአገሪቱ በስፋት እየተዛመተ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ጊዜ በኮሌራ በሽታ የታመሙ ሰዎች ብዛት ከ113 ሺህ 600 በላይ መድረሱ ተጠቅሷል፡፡
ከ3 ሺህ የሚልቁ ሰዎች በበሽታው ሕይወታቸው ማለፉን የአለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
ሱዳን ከ2 አመታት በላይ በመንግስት ጦር እና በRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል በሚካሄድ ውጊያ በጦርነት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡
ጦርነቱ የአገሪቱን ወረርሽኝ የመከላከል አቅም በእጅጉ እያዳከመው መሆኑ ይነገራል፡፡

በማላዊ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ፒተር ሙታሪካ እየመሩ ነው ተባለ፡፡
ሙታሪካ ለፕሬዘዳንታዊ ፉክክሩ ከተሰጠው ድምፅ 66 በመቶውን ማግኘታቸውን የቅድሚያ ውጤቶች እንደሚያሳዩ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ፒተር ሙታሪካ የፕሬዘዳንት ላዛርስ ቻክዌራ የድጋፍ መሰረት የሰፋባቸው ናቸው በተባሉ ግዛቶች ሳይቀር ማሸነፋቸው ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዘዳንት ላዛርስ ቻክዌራ እስካሁን ያገኙ የተረጋገጠ የድምፅ ውጤት ከ24 በመቶ ያልበለጠ ነው ተብሏል፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ የተጠቃለለ ውጤቱን ዛሬ ይፋ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል፡፡
ኮሚሽኑ ውጤቱንም ግልፅ ፣ ትክክለኛ እና ተአማኒ አደርጋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments