መስከረም 12 2018 - ''ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የመድኃኒት አቅርቦት እንዳይቋረጥ እየሰራሁ ነው'' የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት
- sheger1021fm
- Sep 22
- 1 min read
በኢትዮጵያ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን የመድኃኒት አቅርቦት እንዳይቋረጥ እየሰራሁ ነው ሲል የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ተናገረ፡፡
ከዚህ ቀደም በአየር ትራንስፖርት ጭምር መድኃኒት ይቅርብ እንደነበር የተናገረው አገልግሎቱ አሁን በተወሰኑ እንቅስቃሴ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ላይ እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ካሉ ተቋማት ጋር በመሆን መድኃኒት እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንደነገሩን ግጭት ያለባቸው ቦታዎች ላይ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ እንቅስቃሴ በመኖሩ በየብስ ትራንስፖርት የመድኃኒት አቅርቦቱ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከመድኃኒት አቅርቦት ሂደቱ ጋር ተያይዞ በማጓጓዝና ለተጠቃሚዎች እስከሚደርስ ድረስ ጥራቱን ጠብቆ እንዲሆንም የአገልግሎቱ ቅርንጫፎች ጋር ክትትል እንደሚደረግ ዶክተር አብዱልቃድር ተናግረዋል ፡፡
በአጠቃላይ በሌሎችም አካባቢዎችን ላይ ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓት ለማሻሻል የጤና ተቋማት ቀድመው በሚያሳውቁት የፍላጎት መጠን እና በሚገቡት ውል መሠረት መድሀኒት እንዲቀርብላቸው የሚያደርግ አሰራር መጀመሩ ከዚህ በፊት የነበረውን የአቅርቦት ችግር ያስተካክላል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
ለመድሀኒት አቅርቦት እጥረት በተደጋጋሚ ችግር የነበረው ተቋማት በፍላጎታቸው መሰረት ግዥ አለመፈጸማቸው እና በዱቤ የወሰዱትን የመድኃኒት ዕዳ በጊዜ አለመመለሳቸው ሲጠቀስ ነበር አዲሱ አሰራር ይህንን ችግር ያስቀራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ባሉት 19 ቅርንጫፎች በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓት ለማሻሻልም ምዘና እንደሚያደርግ ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








