መስከረም 12 2018 - ''የግል የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ሀላፊዎች መረጃን አለመስጠት፤ ዘርፉን ለጅምላ ፍረጃ ዳርጎታል'' የኢትዮጵያ የግል የከፍተኛ ት/ትና ቴክኒክና ሞያ ስልጠና ተቋማት ማህበር
- sheger1021fm
- Sep 22
- 1 min read
''የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለቤቶችና ሀላፊዎች መረጃን በሚፈለገው ጊዜ አለመስጠት፤ ዘርፉን ለአሉታዊ ጅምላ ፍረጃ ዳርጎታል'' ሲል የኢትዮጵያ የግል የከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሞያ ስልጠና ተቋማት ማህበር ተናገረ።
በማህበሩም ሆነ በመንግስት መረጃ ሲጠየቁ፤ በአግባቡ መረጃ የማይሰጡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሉ ብሏል ማህበሩ።
በዚህ የተነሳም በመንግስት ባለስልጣናት እና በመገናኛ ብዙሀን፤ ዘርፉ በተሳሳተ መልኩ በጅምላ እንዲፈረጅ አድርጎታል ሲልም አስረድቷል።
ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ተቋማት መረጃ ባለመስጠታቸው፤ የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ጭምር ለእንግልት እየዳረጉ መሆኑንም ጠቅሷል።
ማህበሩ ይህንን ያለው ዛሬ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን እያደረገ ባለበት መድረክ ላይ ነው።

በ2017 ዓመት ገጠሙኝ ያላቸው ጉዳዮች ለአባላቱ የዘረዘረው ማህበሩ፤ ዓመቱ ''በአጠቃላይ ሲታይ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጣም ፈታኝ ጊዜ ነበረ'' ብሎታል፡፡
ማህበሩ በትምህርት ሚኒስቴር እና በትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የፀደቁ መስፈርቶች ''በጣም አሳሪ ከመሆናቸው የተነሳ ተቋማት ከዘርፉ ተገፍተው እንዲወጡ ምክንያት'' ሆነዋል ሲልም አስረድቷል።
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በበኩሉ ዘርፉ እንዲመራበት ያዘጋጀሁት መመሪያ አነስተኛ የሚባለውን መስፈርት የያዘ ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲናገር ይሰማል።
በትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የግል ትምህርት ዘርፉን
ለመደገፍ፣ አቅም ለመገንባት ከማህበሩ ጋር ''ተቀራርቦ ለመስራት ያለው ዝግጁነት አናሳ ነው'' ሲል አስረድቷል ማህበሩ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር) በቅርቡ ከግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የእንዴት ትደግፉናላችሁ ጥያቄ ተጠይቀው ድጋፍ ከመጠየቅ የተሻለ የሚሆነው ተዋህደውም ቢሆን ጠንከር እንዲሉ መክረው ነበረ።
የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የሚሰጠው ለግልም ሆነ ለመንግስቶቹ በተመሳይ ወቅት ሆኖ እያለ፤ ለእኛ ውጤቱ ዘግይቶ የሚለቀቅበት አሰራርም አልገባኝም ብሏል።
በ2017 ዓ.ም በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ለዳግም ምዝገባ ተጠርተው ምላሽ ባለመስጠታቸው 84 ተቋማት ከዘርፉ መውጣታቸው መናገሩ የሚታወስ ሲሆን 24ቱ አባላቶቼ ነበሩ ብሏል።
የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማህበሩ አሁን ላይ 150 አባል ተቋማት አሉኝ ሲል ሰምተነዋል።
ማንያዘዋል ጌታሁን












Comments