top of page

መስከረም 12 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Sep 22
  • 2 min read

በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የፊሊፒንስ ዜጎች በአገሪቱ ይፈፀማል ያሉትን ምዝበራ እና ብልሹ አሰራር በመቃወም የአደባባይ ሰልፍ አደረጉ፡፡


ሰልፈኞቹ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ለጎርፍ አደጋ መከላከያ እና መቀነሻ ፕሮጄክቶች ወጪ የተደረገ ከፍተኛ ገንዘብ የምዝበራ ሲሳይ ሆኗል ብለው እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡

ree

ለፕሮጄክቶቹ ዳር ማድረሻ ከመንግስት ከ9.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የምንዛሪ ግምት ያለው ገንዘብ ተመድቦ ነበር ተብሏል፡፡


ሆኖም አብዛኞቹ ፕሮጄክቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ አንዳንዶቹም ከነ ጭራሹ የሌሉ መሆኑ ህዝባዊ ቁጣ መፍጠሩ ተጠቅሷል፡፡


የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ይሄ ሁሉ ገንዘቡ የመዝባሪዎች ሲሳይ ሆኗል እንዲሉ መገፋፋቱ ተሰምቷል፡፡


መንግስት የተቃውሞ ሰልፉ ወደ ግጭት እንዳያመራ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ ባልደረቦችን ማሰማራቱ ታውቋል፡፡



የማላዊ ፖሊስ የምርጫ መረጃ አመሳቅለዋል ያላቸውን 8 የምርጫ ኮሚሽን ሰራተኞች ማሰሩ ተሰማ፡፡


የአገሪቱን መጪ ፕሬዘዳንት፣ የፓርላማ እንደራሴዎች እና የአካባቢ ምክር ቤት ተወካዮችን ለመምረጥ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ድምፅ እንደተሰጠ ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


የምርጫ መረጃን ሆን ብለው አመሳቅለዋል የተባሉት የምርጫው የኮምፒዩተር መረጃ አጠናቃሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡


የኮምፒዩተር መረጃ ማመሳቀሉ የተፈፀመው የትኞቹን የምርጫ ተፎካካሪ ወገኖች ለመጠቀም ወይም ለመጉዳት ታስቦ እንደሆነ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡


ቀደም ሲል የአሁኑ ፕሬዘዳንት ላዛርስ ቻክዌራ እና ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የቀድሞው ፕሬዘዳንት ፒተር ሙታሪካ በየፊናቸው አሸንፈናል እያሉ ነበር፡፡


ሆኖም የምርጫ ኮሚሽኑ ከእኔ በስተቀር ይፋዊ ውጤትን ማንም የማወጅ መብትም ሆነ ስልጣን የለውም ሲል ማስጠንቀቁን መረጃው አስታውሷል፡፡



ኢራን ከአለም አቀፉ የአቶሚክ ተቆጣጣ ኤጀንሲ (IAEA) ጋር ትብብሬን አቋርጫለሁ አለች፡፡


ቴሕራን ከአለም አቀፉ ድርጅት ጋር መተባበሬን አቋርጫለሁ ያለችው በኒኩሊየር መርሐ ግብሯ ምክንያት የተጣለባት ማዕቀብ እንዳይነሳ የፀጥታው ምክር ቤት ድምፅ ከሰጠ በኋላ እንደሆነ አናዶሉ ፅፋል፡፡


ብሪታንያ ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በኢራን ላይ ዳግም ማዕቀቡ እንዲፀናባት ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል ተብሏል፡፡


በተባበሩት መንግስታት መድረክ በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረው ማእቀብ ከ10 አመታት በፊት ተነስቶላት ነበር፡፡


አሜሪካ በፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀዳሚ የአስተዳደር ዘመን ከኒኩሊየር ነኩ ስምምነት መውጣቷ ለኢራን ነገሩን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አድርጎባታል፡፡


ምዕራባዊያ ኃያላን ኢራን የኒኩሊየር ቦምብ ለመስራት እየተሯሯጠች ነው ሲሉ ይከሷታል፡፡


ኢራን ግን መርሐ ግብሬ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እና ለሰላማዊ አገልግሎት የታለመ ነው ብትልም እንዳላመኗት ይነገራል፡፡



በእንግሊዝ ለንደን የሚገኘው ሒትሮ ኤርፖርት ትናንት ለ2ኛ ቀን ባጋጠመው የኮምፒዩር ሥርዓት መናጋት በርካታ መንገደኞች ትናንትናም ለ2ኛ ቀን መጉላላት አጋጠማቸው ተባለ፡፡


በሒትሮ ኤርፖርት መንገደኞች እንግልት የገጠማቸው የመንገደኞች የደህንነት እና የጓዝ ማስተናገጃው የኮምፒዩተር ሥርዓት እክል ስለገጠመው እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በአውሮፓ ከትናንት በስቲያ የተለያዩ ኤርፖርቶችም መሰል ችግር ገጥሟቸው ነበር ተብሏል፡፡


RTX የተሰኘው የአገልግሎቱ አቅራቢ ኩባንያ የኮምፒዩተር ምስቅልቅሎሽ እክል ማጋጠሙን አልካደም፡፡


ሆኖም የእክሉን ምንነት በዝርዝር እንዳላብራራው ተጠቅሷል፡፡


ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያገኝ እተማመናለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page