ሐምሌ 9 2017 - በገቡት ውል መሰረት ግንባታዎችን የማይከውኑ የግንባታ ስራ ተቋራጮችን ፍቃድ ለመንጠቅ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የኮንስትራክሽን ባለስልጣን ተናገረ
- sheger1021fm
- 9 minutes ago
- 2 min read

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ተቆጣጣሪ ተቋም የሆነው ባለስልጣኑ የኮንስትራክሽን ድርጅቶችንና የዘርፉ ሙያተኞችን በመመዝገብ የሙያ ማረጋገጫም ይሰጣል፡፡
ሁሉንም የዘርፉን ተዋንያን የመቆጣጠር ሀላፊነት ቢኖርብንም ባለብን የሰው ሃይል እጥረት ምክንያት ለጊዜው ቁጥጥር የምናደርገው በመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ነው ያሉን በባለስልጣኑ የአማራጭ ግጭት አፈታት ዴስክ ሀላፊ አቶ ትንሳኤ ሙሉ ሸዋ ናቸው፡፡
ከሀላፊው እንደሰማነው ከሆነ እስካሁን ምንም ዓይነት የግንባታ ወቅት ችግር ሲፈጠር የሚታለፈው ግብረ-መልስ በመስጠት ነው በተለይ በሚቆጣጠሯቸው የመንግስት ፕሮጀክት ግንባታዎች አብዛኞቹ የሚሰጣቸው ግብረ-መልሶች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ግን በዲዛይኑ ላይ በሰፈረው መሰረት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች የተመቸ ማድረግን ጨምሮ አንድ የህንፃ ተቋራጭ ከአስገንቢው ጋር በገባው ውል መሰረት ካልሰራና ይህንን ማረጋገጥ ከተቻለ ባለስልጣኑ የሰጠውን የግንባታ ፍቃድ መንጠቅ የሚያስችል መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን አቶ ትንሳኤ ነግረውናል፡፡
የመንግስት ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ የሚወጣላቸውን የግንባታ ዲዛይን ይዘው አይደለም የሚገነቡት፤ ስራው ከተጀመረ በኋላ ዲዛይኑ ይቀየር በሚል ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ስለሚደረግ ከተመደበላቸው በጀት ከፍ ያለ ውጪ እንደሚደረግባቸውና በዚህ ምክንያት ገንዘብ የሚያባክኑ ተቋማት ስለመኖራቸው ተደጋግሞ ይነገራል፡፡
እንዲህ ዓይነት የዲዛይን መለዋወጥ እንዳይኖር ለምን ይሆን ቀድሞ ጥንቃቄ የማይደረገው?
ምክንያታዊ ያልሆኑ የዲዛይን ለውጦች መኖራቸውን እንዴት ነው የምትቆጣጠሩት ያልናቸው አቶ ትንሳኤ የህንፃ ተቋራጮች እስከ 25 በመቶ ድረስ ዲዛይን መቀየር እንዲችሉ ከባለቤቶቹ ጋር የሚገቡት ውል ይፈቅድላቸዋል ብለዋል፡፡
ነገር ግን ዲዛይን ሲደረግ የባለቤቱ ትክክለኛ ፍላጎት ግልጽ ባለመንገድ መቀመጡን እንደሚቆጣጠሩ ነግረውናል፡፡
የግሉንም ይሁን የመንግስት አካላት የሚከውኑትን ግንባታ ልቆጣጠር በህግ ስልጣን አለኝ ሚለው ባለስልጣኑ ባለብኝ የሰው ሃይል እጥረት ለጊዜው የምቆጣጠረው የመንግስት ፕሮጀክቶችን ነው ሲል አስረድቷል፡፡
እነዚህን ስራዎች ለመስራት ከሚያስፈልገው የሰው ሃይል እስካሁን ማማላት የቻለው 65 በመቶውን ብቻ ነው ቀሪውን ለማሟላት በሂደት ላይ ነኝ ብሏል፡፡
በተጨማሪም በግንባታ ውቅት ተገቢውን የግንባታ የደህንነት መስፈርቶች ባለማሟላት በግንባታ ሰራተኞቻ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት እስካሁን በተቋሙ የሚወሰደው የቅጣት እርምጃ በቂ አይደለም አሁን በሚወጣው መመሪያ በዚህም ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡
ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ይዞ ይመጣል ተብሎ ታመነበትን አዲሱን መመሪያ ለማውጣት በዝግጅት ላይ መሆኑን በኮንስትራክሽን ባለስልጣን የአማራጭ ግጭት አፈታት ዴስክ ሃላፊ ከሆኑት ከአቶ ትንሳኤ ሙሉለ ሸዋ ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments