ሐምሌ 8 2017 - የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከ3 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በተጭበረበረ ሰነድ ፓስፖርት ለማውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናገረ
- sheger1021fm
- Jul 15
- 1 min read

ለፓስፖርት በኢሚግሬሽን ቢሮዎች ተራ የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር መቀነሱንም አገልግሎቱ ጠቅሷል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተግባዊ ያደረኳቸው የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያመጡ ነው ብሏል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን የሪፎርም አጀንዳዎች ግምገማ ውጤት አቅርበዋል።
በተጭበረበረ ሰነድ ፓስፖርት ለማውጣት የሚሞክሩ ሰዎችን ለመለየት የተኬደበት ርቀት አንዱ እንደሆነ ዳይሬከተሯ ጠቅሰዋል፡፡
በተጭበረበረ ሰነድ ፓስፖርት ለማውጣት የሞከሩ ከ3 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
ተቋሙ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ፓስፖርት ለማግኘት የሚሞክሩ ሰዎችን የመቆጣጠሩ አቅሙ ያደገው ተቋማዊ ደህንነትን የማረጋጫ ሥርዓትን በመዘርጋቱ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ውጤቱ ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት ጋርም ይገናኛል ብለዋል።
ፓስፖርት ከመስጠት ባሻገር ለጉብኝት እና ለስራ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሰዎች የኢትዮጵያ ቆይታቸው ባሉት መሰረት መሆኑን ለማረጋግጥ የሚያስችል ስራ ተቋማቸው እንደጀመረም ወይዘሮ ሠላማዊት ተናግረዋል፡፡
ለሙከራ በተመረጡ ቀበሌዎች አሰራሩን ከተገበርን በኋላ እያሰፋነው እንሄዳለን ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ የሚወጡ እና ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ዳይሬክተሯ ፤ ተቋማቸውም ይህንኑ የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡
አገልግሎቱ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከአንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት መሰጠቱም ተነግሯል፡፡
በዚህም ለፓስፖርት በኢሚግሬሽን ቢሮዎች ተራ የሚጠብቁ ግለሰቦች ቁጥር መቀነስ ተችሏል የተባለ ሲሆን በቀጣይም ከዚህ በበለጠ እየቀነሰ እንደሚሄድ ተጠቅሷል።
በዚህ ዓመት ወደ ስራ የገባው ኢ-ፓስፖርት አገልግሎት በጎተራ ቅርንጫፍ መሰጠት መጀመሩም ተመልክቷል።
ንጋቱ ረጋሣ












Comments