ሐምሌ 7 2017 - የሰዎችን በተለይ ደግሞ የሴቶችን እርቃን እየቀረፁ ማስፈራሪያ ፣ ገንዘብ ማግኛ የሚዳርጉ ሰዎች መኖራቸው ይነገራል፡፡ ይህ ከሞራልና ከህግ አኳያ እንዴት ይታያል?
- sheger1021fm
- 8 hours ago
- 1 min read
አሁን አሁን የሰዎችን እርቃን በተንቀሳቃሽ ምስል እየቀረጹ ይህ ያክል ገንዘብ የማሠጠኝ ከሆነ በኢንተርኔት ላይ አሰራጫለሁ እያሉ ገንዘብ የሚሰበስቡ እንዳሉ በተደጋጋሚ ተሠምቷል፡፡
ሰዎች ደግሞ የተጠየቁትን ገንዘብ መክፈል ሲያቅታቸው ራሳቸውን እስከ ማጥፋት ሙከራ እንደሚያደርጉም ሰምተናል፡፡
እንዲ አይነቱ ተግባር የሚፈጸመው የእሴት መሸርሸር እና የስነ ምግባር ዝቅጠት ሲኖር ነው ሲሉ በጉዳዩ ላይ የጠየቅናቸዉ ባለሞያዎች ነግረውናል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ አዱኛ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሞያ ናቸው፡፡ የዚህ ችግር መነሻው ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ አንዱ ቢሆንም ገንዘብና ጥቅምን ስህተት ባለው መንገድ ለማግኘት መሞከር ያመጣው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንዲህ አይነቱ ድርጊት የሚያመጣው ቀውስ የአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብን ቀውስ ያስከትላል ሲሉ የነገሩን ባለሞያው ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎችም የወደፊት ህይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቅ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በአደባባይ ነውርን ከሚያለማምዱት በተጨማሪ ይህንን በመከታተል የሚያበረታቱትም ማህበረሰብአዊ ቅጣት ያስፈልጋቸዋል ይላሉ፡፡
አቶ ጥጋብ ደሳለኝ የህግ ባለሙያ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ ማህበራዊ ሚዲያ የሚደረጉትን አጸያፊ ተግባር ለመቆጣጠር ከህጉ በተጨማሪ ሌሎች ተቋማት መስራት እንዳለባቸው ነግረውናል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ እንዲህ አይነቱን የሰዎችን ክብር የሚነካ የጥፋ ድርጊት የሚፈፅሙ ሰዎች በህጉ ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጡ ተቀምጧል፡፡
በዚህ አዋጅ አምስት ሺ እና ከዚያ በላይ ተከታዮች ባሉት የማህበራዊ ሚዲያ ያሰራጨ ወይንም የሚያጋራ ከሆነ ደግሞ ከሃምሳ ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮና የአምስት ዓመት እስር የሚያስቀጣ እንደሆነ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት አዋጅ ላይ ተደግጓል፡፡
ማርታ በቀለ
Kommentare