ሐምሌ 4 2017 - የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፤ የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህንጻ መመረቁ ተሰማ
- sheger1021fm
- Jul 11
- 1 min read
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሆስፒታል ሽፋንን በ1.4 በመቶ ከፍ ያደረገዋል የተባለለት፤ የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህንጻ መመረቁ ተሰማ፡፡
ሆስፒታሉ በክልሉ 12ኛው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሲሆን፣ የሆስፒታል ሽፋንን ከነበረበት ከ32 በመቶ ወደ 33.4 በመቶ ከፍ ያደረገዋል ተብሏል፡፡
ሆስፒታሉን ለመገንባት በ120 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉም ተሰምቷል፡፡
በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ በ120 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህንጻን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዋና ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) መርቀውታል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ የቆንዳን ጨምሮ አራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሆስፒታሉ የተሟላ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ህብረተሰቡ እና የሚመለከታቸው የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ የሕክምና ቁሳቁስ ለማሟላት የሚመለከታቸወን እያስተባበርን ነው ብለዋል፡፡
የገዋታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ኃይሌ፤ የሆስፒታሉ አስፈላጊነት በሕዝቡ በኩል ከ2008 ዓ.ም ሲቀርብ የነበረ ጥያቄ ነው ብለዋል።
አካባቢው ከዞኑ ማዕከል የቦንጋ ከተማ በመራቁ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ትልቅ ችግር ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።
በ13 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን ሆስፒታል ግንባታ በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ አሁን መጠናቀቁ ተነግሯል፡፡
ሆስፒታሉን ጂ ኤንድ ኤስ ቢዩልዲንግ ኮነትራክተር (G & S building contractor plc) መገንባቱ ተጠቅሷል፡፡
ሆስፒታሉ መገንባት በአካባቢው ለሚኖሩ እናቶችና ህፃናት በ84 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኙ የሕክምና ተቋማት ይደረግ የነበረውን የሪፌራል አገልግሎት ችግር በመፍታት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖውን እንደሚቀንስ ተናግረዋል።
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments