top of page

ሐምሌ 4 2017 - የሱዳን ጦርነት በመስጋት ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የገቡ ሁሉም ዜጎች በአንድ መጠለያ እንዲሰባሰቡ ተደርጓል ተባለ

  • sheger1021fm
  • Jul 11
  • 1 min read

በጎረቤት ሱዳን ያለውን ጦርነት በመስጋት ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቡ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በአንድ መጠለያ ጣቢያ እንዲሰባሰቡ ተደርጓል ተባለ።


አሁን ላይ ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መቀነሱንም ሠምተናል።


በጎረቤት ሱዳን ያለው ጦርነት ያሰጋቸው በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች እና በዚያ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያየ ጊዜ ሲገቡ ቆይተዋል።


ጦርነቱን የሰጉ እስከ 47,000 ሰዎች ወደ ክልሉ የገቡበት ጊዜ እንደነበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ አብዱልአዚዝ ተናግረዋል።


ተፈናቃዮቹን በትምህርት ቤቶች እና ድንኳኖች በማቆየት ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን እንዲያገኙ ጥረት ሲደረግ ነበርም ብለዋል።


በትምህርት ቤቶች እና ድንኳኖች ተጠልለው ያሉትን ተፈናቃዮች ወደ ስደተኞች ማቆያ ማዕከል ለማስገባት ሲሰራ እንደቆየም አቶ መሐመድ አስታውሰዋል።


ጥረቱ ተሳክቶም በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የሱዳን ዜጎች በአንድ መጠለያ ማዕከል እንዲሰባሰቡ መደረጋቸውን ነግረውናል።


የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ዕገዛም ከፍ ያለ ነበር ብለዋል።


ጦርነቱን ሰግተው ወደ ክልሉ የገቡ እና በሱዳን የነበሩ ኢትዮጵያዊን ደግሞ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲቆዩ መደረጉን ነው የነገሩን።


ለእነሱም ለዕለት የሚሆን ድጋፍ ከማቅረብ ባሻገር የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እያደረግን ነው ብለዋል።


አሁን ላይ ከሱዳን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገቡ የሀገሪቱ ዜጎችም ሆነ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር መቀነሱን ኮሚሽነሩ ነግረውናል።


ክልሉ በሀገር ውስጥ በገጠሙ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ድጋፍ ለሚሹ ሰዎችም ዕርዳታ እያቀረበ እንደሚገኝ ተነግሯል።


ንጋቱ ረጋሣ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page