ሐምሌ 30 2017 - ''አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያ ከቶውንም አልነቀፈም'' የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ
- sheger1021fm
- Aug 6
- 2 min read
ሐምሌ 30 2017
የአለም የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያ አልነቀፈም፤ በማህበራዊ ትስስር የሚሰራጨው መረጃም ሀሰት ነው ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተናገረ፡፡
የፀጥታ ችግሮች እልባት አለማግኘታቸው፣ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ መካከል ልዩነቱ እየሰፋ መሄዱ፣ የታሰበውን ያህል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አለመገኘቱ፣ እርዳታና ድጋፎች መቀነሳቸውና ሌላውንም በማንሳት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ወደ ኋላ ሊያንሸራትተው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው የአለም የገንዘብ ድርጅት ( #IMF ) ባወጣው ሪፖርት አስረድቶ ነበር፡፡
ይሁንና የባንኩ ገዢ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአለም የገንዘብ ድርጅት ስለ ኢትዮጵያ ማሻሽያ ያለው ምልከታ እጅግ አውንታዊ እንደሆነ ተናግረው በሁሉም ሀገራት ድርጅቱ እንደሚደርገው በኢትዮጵያም ስለሚጋጥም ስጋት ነው ያስቀመጠው ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ የአለም የገንዘብ ደርጅት የኢትዮጵያን የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያ ከቶውንም አልነቀፈም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ገዢው ይህን የተናገሩት ወቅታዊ የውጪ ምንዛሪ ገበያ እንቅስቃሴን በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡
የኢኮኖሚያችን በፍጥነት ማደግ፣ የዋጋ ግሽበት እየረገበ መሄድ፣ የውጪ ምንዛሪ ፍሰት መጨመር በትክክለኛው የእድገት ጎዳና ላይ እንደምንገኝ አመላካች ነው ብለዋል አቶ ማሞ፡፡
የአለም የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ማሻሽያ ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ማሻሻያ በእጅጉ እየነቀፈ እንደሆነ ፤ ከለውጡ የመጀመሪያ ዓመት ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንደሚቀንስ ተደርጎ እየቀረበ ያለ መረጃም ሃሰተኛ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ አሉባልታዎች መሰረተ ቢስ ናቸው ያሉት አቶ ማሞ የገንዘብ ድርጅቱ ስለ ኢትዮጵያ ማሻሻያ ያለው እይታ እጅግ አውንታዊ ነው በሁሉም መስክ የተገኘው ውጤትም ከግምት በላይ እንደሆነ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የዓለም ባንክ በባንኮች የብር የውጪ ምንዛሪ ተመን ላይ ችግር መኖሩን አላነሳም፤ ይልቁኑ በባንኮች ዘንድ ያለውን የብር የውጪ ምንዛሪ ተመን ከኢኮኖሚ መርህ አንፃር በተገቢው ቦታ ላይ እንደሚገኝ፤ የባንኮች የብር የውጪ ምንዛሪ ተመንም በ4.5 በመቶ ከዋጋ በታች እንደሆነ፤ ወይም ብር ከመውረድ ይልቅ ሊጠነክር እንደሚገባ ነው ባንኩ በቴክኒክ ግምገማው ያመላከተው ብለዋል፡፡
ባንኩ ትናንትና አውጥቶ በነበረው የ150 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 28 ባንኮች መሳተፋቸውን የተናገሩት አቶ ማሞ ሁሉም ባንኮች የሚፈልጉትን የውጪ ምንዛሪ አግኝተዋል በአማካኝ አንድ ዶላር በ138 ብር ተሸጧል ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ባንኮች ለንግድ ማህበረሰቡ ያቀረቡት የውጪ ምንዛሪ በእጥፍ ጨምሯል ያሉት አቶ ማሞ ሁሉም ባንኮች በየወሩ 500 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡
ሁሉም ባንኮች ከዛሬ ጀምሮ በቀጣይ ቀናት ለደንበኞቻቸው በበቂ ሁኔታ የውጪ ምንዛሪ እንደሚያቀርቡ በማሳወቅ ላይ ናቸው ያሉት አቶ ማሞ የንግዱ ማህበረሰብም ይህንኑ ተረድቶ በእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን እናበረታታለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አነስተኛ የውጪ ምንዛሪ ፈላጊ መንገደኞች ፍላጎታቸውን የሚያሟሉ የውጪ ምንዛሪ ቢሮዎች አሉ፤ ንግድ ባንክም ለዚህ በቂ ገንዘብ እንደሚያቀርብ አረጋግጧል ብለዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ መደበኛውን የውጪ ምንዛሪ የባንክ ሥርዓት እንዲከተል አጥብቀን እንመክራለን ያሉት አቶ ማሞ ምህረቱ አብዛኞቹ የንግዱ ማህበረሰብ ይህን መንገድ እንደሚከተሉ እናውቃለን ያሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ግን ከመደበኛው ይልቅ ህገ ወጡን ይጠቀማሉ ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ የውጪ ምንዛሪ ተደራሽነትን በተመለከተ በባንኮች ላይ ጥያቄ ያነሳል ያሉት ገዢው ወደ ጥቁር ገበያው የሚሄዱትም ከባንኮች በበቂ የውጪ ምንዛሪ ስለማያገኙ እንደሆነ ይናገራሉ ብለዋል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ጥያቄዎች አሁን በአብዛኛው ምላሽ እንዳገኙ በባንኩ ገዢ መግለጫ ተመላክቷል፡፡
ከባንኮች የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት ረጅም ጊዜ ይፈጃል እየተባለ የሚቀርበውን ቅሬታ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ባንኮች ይህን አሰራር ለማሳጠር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የባንክ ስርዓቱን የማይጠቀሙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በአፋጣኝ በባንክ ሥርዓት እንድተገለገሉ እናሳስባለን ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
ብሔራዊ ባንክ ወደ ትይዩ የሚገባን እና ሚዘዋወረውን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚከታተልበት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ዘርግቷል ያሉት አቶ ማሞ ምህረቱ በህገ ወጥነት የሚገለገሉ አካላት ከድርጊታቸው ካልታቀቡ ገንዘባቸውን እስከመውረስ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s
Comments