top of page

ሐምሌ 30 2017 - ታሪክን የኋሊት - አሜሪካ መቶ ሺዎችን የጨረሰውን አቶሚክ ቦንብ በጃፓኗ ሂሮሽማ ላይ የጣለችው በ1937 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር

  • Aug 6, 2025
  • 2 min read

አሜሪካ መቶ ሺዎችን የጨረሰውን አቶሚክ ቦንብ በጃፓኗ ሂሮሽማ ላይ የጣለችው በ1937 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡

 

አቶሚክ ቦምቡን በጣለችበት ያኑ እለት ከ150,000 ሰዎች በላይ በአልተለመደና በአሰቃቂ አሟሟት ወደትቢያነት ተለወጡ፡፡

 

በአቶሚክ ቦንቡ ሰበብ ቆስለውና ተጠቅተው የነበሩ 60 ሺህ ሰዎች በሚቀጥሉት 5 ወራት ረገፉ፡፡

 

35,000 ያህል ቆስለው በፅኑ ደዌ ተጠቁ፡፡

 

የአቶሚኩ ጨረር ተጠቂ የሆኑትና ሰውነታቸው ያገኛቸው፣ በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ዳርጓቸው ተሰቃይተው ኖረዋል፡፡

 

ከ1930ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ፣ አሜሪካ በከፍተኛ ሚስጢር የአቶሚክ ቦምብ ስትሰራ ቆየች፡፡

 

የተሳካ ሙከራ ካደረገች በኋላ፣ በጃፓን ላይ እንዲጣል የወቅቱ ፕሬዘዳንት ሃሪይ ትሩማን አዘዙ፡፡

 

አሜሪካ ጃፓን ላይ አቶሚክ ቦምብ በጣለችበት ወቅት፣ ጀርመን ተሸንፋ በአውሮፓ ያለው የሁለተኛው የአለም ጦርነት፣ አብቅቶ ነበር፡፡

 

ጃፓን ግን፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ ጦርነቱን ቀጠለች፡፡

 

አሜሪካ፣ ጃፓንን በእግረኛና በአየር ሀይሏ ለመውረር ብትፈልግ፣ ከፍተኛ እልቂት እንደሚጠብቃት፣ የፕሬዘዳንት ትሩማን አማካሪዎች አማከሩ፡፡

 

በሌላ በኩል የኮሚኒስቷ ሶቪየት ህብረት በጦርነቱ በአሸናፊነት መውጣት ለመስፋፋት የልብ ልብ እንዳይሰጣት ለማስጠንቀቅም ነው ተብሏል፡፡

 

ስለዚህ፣ አዲሱን ቦምብ ተጠቅሞ ጦርነቱን ቶሎ የማጠናቀቁን አስፈላጊነት ትሩማን አመኑበት፡፡

 

ሐምሌ 29/1937   15,000 ቶን ክብደት ያለውና ትንሹ ልጅ ብለው የሰየሙትን አቶሚክ ቦንብ በሂሮሽማ ላይ አዘነበች፡፡

 

ይህ ማለት የማጥፋት አቅሙ 15 ሚሊዮን ኪግ ከሚመዝኑ ቦምቦች የሚበልጥ ነበር፡፡

 

ቦምቡ የሂሮሽማን ከተማ በአምስት ስኳየር ኪሎ ሜትር ስፋት፣ ምልክት ሳይተው እንዳልነበረች አድርጎ አወደማት፡፡

 

ከሶስት ቀናት በኋላ፣ በሌላዋ የጃፓን የወደብ ከተማዋ ናጋሳኪ ላይ፣ አሜሪካ ተመሳሳይ የአቶሚክ ቦምብ ጣለች፡፡

 

40,000 የሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች በሰኮንዶች ውስጥ ፀጥ አሉ፡፡

 

የአቶሚክ ቦምብ ናዳ የወረደበት የጃፓን መንግስት፣ ያለምንም አስገዳጅ ጥያቄ እጁን ሰጠ፡፡

 

በጃፓን የደረሰው የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የሁለተኛው የአለም ጦርነት አስቁሟል፡፡

 

ግን፣ አለም ሰላም ያጣችበት የቀዝቃዛው ጦርነት መጀመሪያ ሆነ፡፡

 

ነግ በኔ ያለችው ሶቪየት ህብረት፣ ቀመሩን ከአሜሪካ አስርቃ የኒዮክለር ቦምብ ባለቤት ሆነች፡፡

 

ሌሎች ሃገሮች ፈለጉን ስለተከተሉ ፣ አለም በቅራኔ ውስጥ ባሉ ሃገሮች ፍጥጫ በኒዩክለር ቦምብ ስጋት ላይ ወደቀች፡፡

 

አሜሪካ በሂሮሺማ ላይ የአቶሚክ ቦምብ ጥላ ህዝቡን ከፈጀች ዛሬ 90 ዓመት ሆነ፡፡

 

እሸቴ አሰፋ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page