ሐምሌ 3 2017 - የገቢ ግብር ማሻሽያ ረቂቅ አዋጅ
- sheger1021fm
- Jul 10
- 3 min read
የገቢ ግብር ማሻሽያ ረቂቅ አዋጁ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለባቸውን የግብር ጫና መቀነስ አንዱ አላማው ቢሆንም፤ በውስጡ የያዛቸው ድንጋጌዎች ግን እሱን አንደማያመለክቱ እንደራሴዎች ተናገሩ፡፡
ረቂቅ አዋጁ በአለም ባንክ መስፈርት መሰረት የድሃ ድሃን የገቢ ግብር የሚያስከፍል ነው በሚል ተተችቷል፡፡
አንድ ሰው ከ30,000 ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ማንኛውንም ነገር ከተገበያየ መቶ በመቶ እጥፍ ቅጣት እንዲከፍል የገቢ ግብር ማሻሽያ ረቂቅ አዋጅ ያስገድዳል፤ ይህም በፓርላማ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
እንደራሴዎቹ በረቂቅ አዋጁ ላይ ትችት እና ቅሬታ ያቀረቡት ትናንት ከሰዓት በኋላ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በገቢ ግብር ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት አንድ የምክር ቤት አባል በማሻሻያው ላይ የቀረበው፤ ሰራተኛ ከሚያገኘው ወርሃዊ ደመወዝ ላይ ተቆራጭ የሚደረግበት መነሻ የግብር ምጣኔ ምንን መሰረት ተደርጎ እንደተወሰነ ለእኔ ግልጽ አልሆነልኝም ብለዋል፡፡
ቢያንስ በደመወዝ ማሻሻያው በተደረሰበት ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን 4570 ብር ያለውን ለምን ከታክስ ነጻ መደረግ እንዳልተቻለ የጠየቁት የምክር ቤት አባሉ ለምን ከ2000 በላይ የሚያገኙ ተቀጣሪ ሰራተኞች የገቢ ግብር እዲከፍሉ ተደረገ? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ለሚያገኘው ሰራተኛ እኛ እና የገንዘብ ሚኒስቴር ነን እንጂ የምናስብለት ሌላ አካል ያለ አይመስለኝም ያሉት ተወካዩ ለምን የግብር መነሻ ከገንዝብ የመግዛት አቅም ጋር የሚመጣጠን አልሆነም? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ገቢ እንዳይቀርብን እንፈልጋለን ያሉት እንደራሴው ግን ገቢውን ማሳደግ ያለብን በዚህ መንገድ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡
አስተዳደራዊ ክፍሉን በአግባቡ ከያዝን ማካካስ አይቻልም ወይ ሲሉ የጠየቁት የምክር ቤት አባሉ ይሄ ነገር ቅሬታ ያስነሳብናል ይሄን እንዴት አይታችሁታል? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
መሆን የሚገባውን ነው ማድረግ ያልብን ያሉት የምክር ቤት አባሉ እኔ እያልኩ ያለሁት ዝቅተኛውም ሰው አይጎዳብን፣ የመንግስት ገቢም መቅረት የለበትም ነው ብለዋል፡፡
አቶ ወንደሰን አድማሴ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ግብር መክፈል ያለበት ማነው? የሚል ጥያቄ ከጠየቁ በኋላ የድሃ ድሃ ወይም ( #Absolute_Poverty ) ውስጥ ያለ ሰው ግብር መክፈል አለበት ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2022 በአለም ባንክ በተሰራ ጥናት አንድ ሰው በቀን ከ2.15 ዶላር በታች የሚያገኝ ከሆነ ድሃ እንደሆነ ያሳያል ያሉት አቶ ወንደሰን፤ የኢትዮጵያውን ግን አሁን ባለው የምንዛሪ ተመን ከዚያ ከፍ ያለ ስለ ሆነ absolute poverty ውስጥ ያለ ሰው ግብር መገበር አለበት ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤት አባሉ እና ቋሚ ኮሚቴው የጠየቀው ጥያቄ በጥሬ ገንዘብ ግብይት ላይ የተጣለውን ገደብ የተመለከተ ነው፡፡
በማሻሽያ ረቂቅ አዋጅ መሰረት ከ30,000 ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ግብይትን የሚከለክል ሲሆን ሲገበያይ የተገኘ ሰው ደግሞ የከፈለውን ገንዘብ በእጥፍ እንዲከፍል ያስገድዳል፡፡
በዚህ ላይ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ወንደሰን ይህን ክፍል በተመለከተ ተሞክሮ የተወሰደባቸው ሀገራት ከእኛ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደሉም ብለዋል፡፡
ተሞክሮው የተወሰደው ከህንድ እና ከቱርክ ነው የእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ከእነሱ ጋር ይጣጣማል ወይ ከእኛ ጋር የሚመሳሰሉ ሀገራት ተሞክሮ ምንድን ነው የሚመስለው? ሲሉ የጠየቁት የምክር ቤት አባሉ ከእኛ መሰረተ ልማት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ማየት ቢቻል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የገንብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የግብር ምጣኔውን ወደ 2,000 ከፍ እንዲል ሲደረግ መንግስት ከፍተኛ ገቢ ያጣበት ግን ደግሞ ዜጎችን ከማህበራዊ ግብ አንጻር በጣም ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡
ማሻሽያው መንግስትን ገቢ ቢያሳጣንም ዜጎቻችንን ግን ሊጠቅም ይችላል በሚል የተወሰነ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
በየደረጃው ላይ ማሻሽያ እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ቆይቶ የመጣ ጥሩ ማሻሻያ አድርገን ልንወስደው ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አዋጁ በቀጣይ የዜጎች የገቢ ሁኔታ እየታየ የሚሻሻል እንደሆነም እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በጥሬ ገንዘብ ግብይት ላይ የተጣለ ገደብን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ዋሲሁን አባተ ናቸው፡፡
አቶ ዋሲሁን በምላሻቸው በዚህ አዋጅ የተቀመጡ ድንጋጌዎች የሚመለከተው የፌዴራል ግብር ከፋይዎችን እንደሆነ ተናግረው በታክስ ላይ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮችን የገንዘብ ገደቡ ለመከላከል እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡
ይህን መሰል አሰራር በብዙ ሀገሮች እንደሚሰራበት የተናገሩት አቶ ዋሲሁን የታክስ ማጭበርበር ክልሎች የገንዘብ ገደቡን እንደየ ሁኔታቸው የራሳቸውን ህግ እንዲያወጡ ይፈቅዳል ብለዋል፡፡
ኔትዎርክ እና ሲስተም በማይሰራበት አካባቢ በጥሬ ገንዘብ ግብይት የሚፈጸምበት ሁኔታ እንዲኖር በመመርያ የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚፈቅድ አቶ ዋሲሁን አስረድተዋል፡፡
የፌደራል የገቢ ግብር ማሻሽያ ረቂቅ አዋጅ በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ ከተሰጡ መብቶች ውጪ በሌሎች አዋጆች፣ ደንቦች እና መመርያዎች የተሰጡ የገቢ ግብር ነጻ መብቶችን የሚሽር ነው ተብሏል፡፡
በግብር ማስከፈያ ሰንጠረዦች ላይ በተደረገው ለውጥ ምክንያት መንግስት ከሀገራዊ ጠቅላላ ምርት 0.21 በመቶ ያጣል ተብሏል፡፡
ከዚህ በላይ ማስተካከያ ይደረግ ቢባል በመንግስት አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ውጤትን አንደሚያስከትል ተነግሯል፡፡
በሚደረገው ማሻሻያ ምክንያት የሚታጣውን ገቢ፤ የግብር መሰረትን ለማስፋት በአዋጁ በተወሰዱ ማስተካከያዎች እና የታክስ አስተዳደሩን ውጤታማ በማድረግ ማካካስ እንዲሚቻል ታምኖበታል።
በረቂቅ ላይ ባለው የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት በመቀጠር በሚገኝ ወርሃዊ ገቢ ላይ ለሚጣለው ግብር ተፈጻሚ የሚሆኑት መጣኔዎች ፦
በየወሩ ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ (ብር) በመቀጠር በሚገኝ ገቢ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን መጣኔ
0 -2,000 0%
2,001-4,000 15%
4,001-7,000 20%
7,001-10,000 25%
10,001 -14,000 30%
ከ14,000 በላይ 35%
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments