top of page

ሐምሌ 25 2017 - የኢትዮጵያ 97 በመቶ ገቢና ወጪዋ “በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር “ የሚተላለፍ በመሆኑ ይህ መስመር በብርቱ መጠናከር አለበት ተባለ።

  • sheger1021fm
  • Aug 1
  • 3 min read

የኢትዮጵያ 97 በመቶ ገቢና ወጪዋ ወይም አጠቃላይ ንግዷ “በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር “ የሚተላለፍ በመሆኑ ይህ መስመር በብርቱ መጠናከር አለበት ተባለ።


ይህን የተናገሩት የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ናቸው።


ገዥው ኤክፖርትን ማበረታታት ከፈለግን ወደ ኋላ የቀረውን የሎጀስቲክስ ስራ ቅድሚያ ማሻሻል አለብን ብለዋል።


የሎጀስቲክስ ችግሩን በሥርዓቱ ማስተካከል ማለትም ፤ የፋይናንስ ሥርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ ነው፤ ኤክስፖርቱን ማሻሻል ማለትም የውጭ ምንዛሪውን ለውጦ የፋይናንስ ሥርዓቱንም ከፍ ማድረግ ነው ሲሉ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ የአፍሪካ ንግድ ቀጠና አባል እንደመሆኗ ፤ በሁሉም የጎረቤት ሐገሮች በባቡር ለማስተሳሰር መንገድ ጀምራለች ተብሏል።


ንግድንና ኢኮኖሚን ከፍ ለማድረግ ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር ማለትም ኢትዮዽያን ከሱዳን ፤ ከኬንያ ፤ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ጋር በባቡር ትራንስፖርት ለማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን ሰምተናል።


ይህ የተሰማው ዛሬ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በመከረበት ጊዜ ነው።


በዚሁ ጉባኤ የኢትዮ -ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈፃሚ ታከለ ኡማ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር አህመድ ሽዴ ፤ ለትራንስፖርት ሚኒስትር አለሙ ስሜ እና ለብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ፤ የባቡር መሰረተ ልማት ፋይዳ በፋይናንስ በኢኮኖሚ፤ በንግድና ቀጠና ጋር በተገናኘ ተያያዥ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል።


ቅድሚያ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ከፍ ለማድረግ የባቡር መሰረተ ልማትን እንዴት ማሳደግ ይቻላል?፤ ተብለው የተጠየቁት የገንዘብ ሚንስቴር አህመድ ሽዴ ፤ በቅድሚያ በሁለቱ ሀገሮች የተሰራው የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ፕሮጀክት ለ ኢኮኖሚው የተሻለ እንዲያዋጣ በብርቱ እየተሰራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ree

የባቡር ስራ ትልቅ የፋይናንስ አቅርቦት ይፈልጋል ያሉት አህመድ ሽዴ ፤ በጅቡቲ ወደብ ያለውን ከፍተኛ ጭነት በማመላለስ ይህን መሰረተ ልማት በብርቱ እያገዘ ነው ብለዋል።


ኢትዮጵያ የአፍሪካ ንግድ ቀጠና አባል እንደመሆኗ፤ የንግድ እንቅስቃሴውን ለማገዝ ባቡር ቀዳሚ መሰረተ ልማት በመሆኑ ፤ በሁሉም መአዘን መሰረተ ልማቱን ከፍ ለማድረግ ትኩረት እናደርጋለን ብለዋል።


የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ፤ እያደገ በመምጣቱ ከጎረቤት ሐገሮች ጋር የሚያስተሳስር የባቡር መስመር ያስፈልጋል ወደ ፊትም ይሰራል ብለዋል።


አህመድ ሽዴ ጨምረውም የተጀመሩ የባቡር ፕሮጀክቶችንም ለመጨረስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።


የኢትዮ - ጅቡቲ ምድር ባቡር የሐገሪቱን ወጭ ገቢ እቃና ኢኮኖሚ የበለጠ እንዲሸከም የገንዘብ ሚኒስቴር በብርቱ እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።


ሚኒስትሩ የኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ነዳጅ ለማመላለስ የጀመረውን ፕሮጀክት ሲጨርስ ከወደብ ወደ መሀል ሐገር የሚገባውን ነዳጅ አቅሙን አሳድጎ በብርቱ ያመላልሳል ብለዋል።


ሌላኛው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የገንዘብ ሥርዓት ለማሳካት ፤ የባቡር መሰረተ ልማቱን በምን መደገፍ ይበጃል? ምንስ ያግዛል ? ተብለው የተጠየቁት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ለኢትዮዽያ ኢኮኖሚ የሚኖረው ፋይዳ ብዙ ነው ብለዋል።


የኢትዮ - ጅቡቲ ምድር ባቡር መሰረተ ልማት ለመገንባት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ብድር ወስዳለች አሁንም እየከፈለች ነው ያሉት ማሞ ምህረቱ ፤ መሰረተ ልማቱ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ብዙ መሰራት አለበት ብለዋል።


የ ኢትዮ - ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈፃሚ ታከለ ኡማ የሎጅስቲክስ ዘርፋ ከፍ እንዲልም ፤ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንዲያመጣ በብርቱ ተሰርቷል ካሉ በውኋላ ለትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚንስቴር ሚኒስትር አለሙ ስሜ ነገሮች የበለጠ እንዲሻሻሉ ምን ላይ መበርታት ያስፈልጋል ሲሉ ጥያቄ አቀርበውላቸዋል።


ሚኒስትሩ የባቡር ትራንስፖርት ኢኮኖሚን ከማሳደግ ባለፈ ፤ ሸቀጦችን በብዛት ፤ በፍጥነት እና በእርካሽ ዋጋ ለማጓጓዝ ይበጃል ካሉ በውኋላ ፤ ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ከምታስገባው ገቢና ወጭ እቃ መሀል ወደ ውስጥ የምታስገባው የፍጆታ እቃ ቀንሷል ሲሉ አስረድተዋል።


የካፒታል እቃ ግን መግባት ጨምሯል ፤ ያሉት አለሙ ስሜ ፤ ወደ ውስጥ የሚገባው በመጠን ቀንሶ ወደ ውጭ የሚላከው በመጨመሩ የንግድ ሽርክናን በማሳደግ የባቡር መሰረተ ልማቱን አቅም ከፍ ለማድረግ በብርቱ እየተሰራ ነው ብለዋል።


ጉባኤው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ከአካባቢው ጋር አብራ ለማደግ እንደባቡር ያሉ መሰረተ ልማቶችን እንዴት ትበርታበት በሚለው ሲመክር ውሏል።


ኢትዮጵያ የንግድ እና ኢኮኖሚን ከፍ ከማድረግ ባለፈ ፤ የተለያዩ አካባቢዎችን በማስተሳሰር ንግድንም ለማቀላጠፍ የባቡር መስመሯን ተጠቅማ ፤ እንዴት የፋይናንስ ሥርዓቷን ትለውጥበት በሚለው ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ሰፋ አድርገው መክረዋል።


የ ኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ የመተላለፍያ ጊዜን በመጨመር እና አቅምን በመፈተን፤ ለረጅም ግዜ የንግዱን እና አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ሲፈትን ቆይቷል።


የዛሬው ጉባኤውም የኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር መሰረተ ልማት ሙሉ ለሙሉ ጉልበቱን ተጠቅሞ ፤ ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ያግዛል መባሉን ሰምተናል።


ተህቦ ንጉሴ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Recent Posts

See All
ጥቅምት 20 2018 - የፍትህ ስርዓት ችግር ምክንያት ስራው ላይ እክል እየገጠመው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ

የሚሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦች ያለ በቂ ምክንያት የማይፈፅሙ ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ቢሞክርም ባለው የፍትህ ስርዓት ችግር ምክንያት ስራው ላይ እክል እየገጠመው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ፡፡ ተቋሙ የአስተዳደር በደል ደረሰብን እምባችን ይታበስልን የሚሉ አቤት ባዮችን ቅሬታ በመቀበል

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page