top of page

ሐምሌ 25 2017 - እስከ ምሽት 3፡30 አልሰራችሁም የተባሉ 366 የንግድ ተቋማት ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

  • sheger1021fm
  • Aug 1
  • 1 min read

ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የምሽት የንግድ ስራን ለማስፈፀም የወጣው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደተግባር መግባቱ ሲነገር ቆይቶ አሁን ወደ እርምጃ መግባቱን ሰምተናል፡፡


ደምቡን ከሚያስፈፅሙ ቢሮዎች መካከል አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ የከተማዋ የምሽት የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ቅኝት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል፡፡


በቅኝቱም የንግድ ስራቸውን ለተገልጋዩ ምሽቱን ክፍት አድርገው ማስተናገድ ሲገባቸው ከ3፡30 በፊት ሱቃቸውን በመዝጋት ደምቡን ተላልፈዋል ላላቸው 276 ነጋዴዎች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡


በሌላ በኩል ማንኛውም በመንገድ ዳር ላይ የሚገኝ የንግድ ተቋም ወይም አገልግሎት ሰጪ ተቋም ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ የተቋሙን የውጭ እና የውስጥ መብራት ማብራት አለበት፤የሚለውን በመተላለፍ ሆን ብለው መብራት አጥፍተዋል ያላቸው 90 ነጋዴዎች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ መወሰዱን የነገሩን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ናቸው፡፡


ቢሮው ከሰሞኑ በሰጠን መረጃ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው የአፈፃፀም መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ወደ ቅጣት አንገባም ብሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ወደ ቅጣት ገብቷል፡፡


አሁን ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው የንግድ ተቋማት በድርጊታቸው ከቀጠሉ ወደ ቀጣዩ እርምጃ ማለትም ወደ ገንዘብ ቅጣረት እሸጋገራለሁ ብሏል፡፡


በደምቡ እስከ ምሽት 4ሰዓት እንዲሰሩ ግዴታ የተጣለባቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚደረገው መሰል ቁጥጥር በከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ እየተደረገ ነው ያሉን ሃላፊው ደምቡን አክብረው ካልሰሩ እርምጃው እነርሱም ላይ ይቀጥላል ሲሉም አስረድተዋል፡፡


ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ደምብ ባንኮችንም ይመለከታል ያለው ቢሮው ለጊዜው የበር ለበር ቁጥጥር እየተደረ ያለው በንግድ ቤቶች ላይ ነው፤የማስፈፀሚያ መመሪያው ሲወጣ ባንኮችም እስከ ምሽት ለመስራት እንደሚገደዱ ጠቅሶ አብዛኞቹ ፍቃደኛ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡


የሰዓት ገደቡ በሥራ ባህሪያቸው ምክንያት 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ወይም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንደማይመለከት ከደምቡ ላይ ተመልክተናል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ……


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page