ሐምሌ 24 2017 - የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ላይ አሁንም ብዙ የሚቀረው ነው ተባለ።
- sheger1021fm
- Jul 31
- 1 min read
የታየው አነስተኛ ሽግግርም ከግብርና ወደ አገልግሎት መሆኑ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ ተነግሯል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ዙሪያ “ከአፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል” ጋር በመሆን ያካሄደውን ጥናት ውጤት ዛሬ በሃይሌ ግራንድ ሆቴል ይፋ አድርጓል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ባለፉት 20 ዓመታት የነበረውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ፤ ዕድገቱ ያመጣቸውን ውጤቶችና፤ መዋቅራዊ ሽግግሩን በተመለከተ፤ ከአፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል* ጋር በመሆን ያካሄደውን ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል።
ኢኮኖሚው ባለፉት 20 ዓመታት እያደገመ መምጣቱን የጠቀሰው ጥናቱ መዋቅራዊ ሽግግሩ ግን ብዙ የሚቀረው ነው ብሏል።
ግብርና ለጥቅል ሀገራዊ ምርት ወይም ጂ ዲ ፒ የሚያበረክተው ድርሻ በትንሹ እየቀነሰ ቢሆንም አሁንም ከፍ ያለው አስተዋጽኦ የእሱ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል።
መዋቅራዊ ሽግግሩ ከግብርና ወደ አገልግሎት ዘርፍ መሄዱም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር አለበል ባይሩ ተናግረዋል።
ግብርና ፤ አገልግሎት እና አምራች ዘርፎች በየራሳቸው ያሳዩት ዕድገትም ቢሆን ከሌሎች ሀገራት አንጻር አነስተኛ እንደሆነ ዶክተር አለበል ተናግረዋል።
በተለይ ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲመሳከር ሶስቱም ዘርፎች እያደጉ የመጡበት መጠን ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
ጥናቱ የዳሰሰው ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ዓመታት የምታመርታቸውን እና ወደ ውጪ የምትልካቸውን ምርቶች በምን ያህል መጠን አብዝታለች የሚለው ነው።
በዚህም ረገድ ዕድገት ያሳዩት የግብርና ምርቶች መሆናቸው ተጠቅሷል። አምራች ዘርፉ ጥቂት የሚባል ለውጥ እንዳሳየ ነው ዶክተር አለበል የነገሩን።
የግብርና ምርታማነት ዕድገትም ቢሆን በተወሰኑ አይነቶች ብቻ የሚገለጽ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አምስት የግብርና ውጤቶች ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች እስከ 77 በመቶውን መሸፈናቸው የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከግብርና ውጤቶችም ቡና ከኢትዮጵያ የወጪ ምርት ከ35 በመቶ የሚበልጠውን ድርሻ እንደሚሸፍን፤ የሀገራችን ከፍተኛ የገበያ መዳረሻ ተብለው የሚታወቁ ሀገራትም ከአስር እንደማይበልጡ ጥናቱ ጨምሮ አሳይቷል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments