የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለውይይት በቀረቡት ስምንቱም አጀንዳዎች ላይ በተጀመረው ምክክር ከስምምነት ተደርሶ ሊጠናቀቅ ይችላል የሚል እምነት እንደሌለውና፣ አንዳንድ አጀንዳዎች ለቀጣይ ትውልድ ሊተላለፉ እንደሚችሉ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተናግሯል።
- 2 hours ago
- 2 min read
ነሐሴ 4 2018
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለውይይት በቀረቡት ስምንቱም አጀንዳዎች ላይ በተጀመረው ምክክር ከስምምነት ተደርሶ ሊጠናቀቅ ይችላል የሚል እምነት እንደሌለውና፣ አንዳንድ አጀንዳዎች ለቀጣይ ትውልድ ሊተላለፉ እንደሚችሉ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተናግሯል።

የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር እየተካሄደ ባለው ምክክር «ሐሳቤ ካልተደመጠ ጥዬ እሄዳለሁ» ማለት ተገቢ አይደለም ብለዋል።
በስምንቱም አጀንዳዎች ላይ ባይሆንም በተወሰኑት አጀንዳዎች ላይ በእርግጠኝነት «ጥሩ» የምክረ ሐሳቦች ይዘን እንቀርባለን የሚል እምነት አለን ያሉት ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፣ አንዳንዶቹ ሊዘገዩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ኮሚሽነሩ ይህን ያብራሩት የምክክሩን ሂደት አስመልክተው ዛሬ ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው፡፡
እየተካሄደ ባለው ምክክር በሁሉም አጀንዳዎች ላይ የሚመክሩ ቡድኖች እኩል በተያዘላቸው ጊዜ እየሄዱ እንዳልሆነ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
«እስከ ነገ ከሰዓት ድረስ ግን ሁሉም ቡድኖች 500 አባላት ወዳሉት የቡድን ውይይት ያልፋሉ ብለን እንጠብቃለን» ሲሉም አክለዋል፡፡
በመካሄድ ላይ ባለው ምክክር በተለይ በፌደራል ከተሞች አጀንዳ ሥር በአዲስ አበባ ጉዳይ እየመከሩ ያሉ ተመካካሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ክርክር መኖሩን ነግረውን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ሌሎች ተመካካሪ ቡድኖች ያጠናቀሯቸውን አጀንዳዎች 500 አባላት ላሏቸው ቡድኖች ሲያቀርቡ፣ በአዲስ አበባ ሥር የሚመክሩ ተመካካሪዎች ግን «ከተማዋ የኦሮሚያ ዋና ከተማና መቀመጫ መሆኗ በሕገ መንግሥቱ ይደንገግልን» በሚሉና «ይህ በፍጹም መሆን የለበትም» በሚሉ ተመካካሪዎች መካከል አለመስማማት በመፈጠሩ ለሌላ ቀን ቀጥረው ተበትነው ነበር፡፡
በከተማዋ ጉዳይ የሚመክሩ ተመካካሪዎች ጉዳዩ በጣም አከራካሪ መሆኑን ተናግረው፣ በቅርቡ ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡
አንዳንዶች የከተማዋ ጉዳይ ቢዘገይ ይሻላል የሚል እምነት እንዳላቸው የጉዳዩ ተመካካሪዎች ጠቅሰዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በበኩላቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ «እየተካሄደ ባለው ምክክር “ሐሳቤ ካልተደመጠ ጥዬ እሄዳለሁ” ማለት ተገቢ አይደለም። የምክክር ባህል ስለሌለን አንዳንዶቻችን አቋማችንን በጉልበትም ጭምር ነው ወደፊት ማምጣት የምንፈልገው» ካሉ በኋላ፣ «'ይህ ካልተደረገልኝ ይህን አደርጋለሁ'፣ 'ካልሰማኸኝ ጥዬህ እሄዳለሁ' ማለት ተገቢ አይደለም፤ እዚህ የመጣነው ጥሎ ለመሄድ አይደለም» ብለዋል፡፡
«እዚህ ስንመጣ አቋማችንንና አስተሳሰባችንን ከሌሎች ጓደኞቻችን፣ እህት ወንድሞቻችንና ወላጆቻችን ጋር ወደ ማህል በማምጣት ሁላችንም አሸናፊ እንድንሆን ነው» ሲሉ አብራርተዋል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፣ «አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ነው 'ካልሰማኸኝ ጥዬ እወጣለሁ' የሚባለው።»
«በስምንቱም ባይሆንም በተወሰኑት አጀንዳዎች ላይ በእርግጠኝነት ጥሩ የምክረ ሐሳቦች ይዘን እንቀርባለን የሚል ተስፋ አለን» ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ «ቢቻል በአብዛኞቹ ላይ፣ ወይም በሁሉም ላይ፤ አለበለዚያ ግን የተወሰኑት አጀንዳዎች ሊያድሩ ይችላሉ፤ የተወሰኑት ግን ሊፈቱ ይችላሉ።
ሁሉንም ማለትም ስምንቱንም ጨርሰን እንወጣለን የሚል እምነት የለንም፤ አንዳንዶች ጊዜ ይፈጃሉ» ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ የትኞቹ አጀንዳዎች ሊዘገዩ አንደሚችሉ ወይንም በየትኞቹ አጀንዳዎች ላይ ከስምምነት ተደርሶ ምክረ ሀሳብ ሊሰጥ እንደሚችል በመገለጫቸው ያሉት ነገር የለም፡፡
ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው «እዚህ የመጣነው ከየመንደራችን ይዘን የመጣነውን ጥያቄ ለመመለስ አይደለም፤ እዚህ የመጣነው ሀገራችንን ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገን መሆን አለበት» ሲሉ ለተሳታፊዎች፣ ለአስተባባሪዎች እንዲሁም በምክክሩ ላይ ለነበሩ አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
«እስካሁን ድረስ አንድም ውሳኔ በአንድም አጀንዳ ላይ አልተሰጠም፤ ምናልባትም ወደፊትም አይሰጥም፣ የሚሰጠው ምክረ ሐሳብ ነው» ብለዋል ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፡፡
ያሬድ እንዳሻው
_edited.jpg)


Comments