ሐምሌ 24 2017 - የባህላዊ ህክምና ዘርፍ ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሀገር በቀል ጨምሮ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዕጽዋት ከመጥፋት መታደግ ያስፈልጋል ተባለ
- sheger1021fm
- Jul 31
- 1 min read
በኢትዮጵያ ከዘመናዊ ህክምና ባልተናነሰ የሚሠራበት የባህላዊ ህክምና ዘርፍ ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሀገር በቀል ጨምሮ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዕጽዋት ከመጥፋት መታደግ ያስፈልጋል ተባለ፡፡
በብዛት በሚበቅሉባቸው አካባቢዎች ላይ መመናመንና የመጥፋት ስጋት ያለባቸው #ሀገር_በቀል_ዕጸዋት መኖራቸውን የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ተናግሯል፡፡
ሀገር በቀል ሆነው በተለይ በኢትዮጵያ የአየር ፀባይ የሚበቅሉ እጽዋት ቁጥር ተለይተው በሚበቅሉባቸው አካባቢዎች ላይ እየተመናመኑ መምጣታቸውንና ለመጥፋትም እንደተቃረቡ የለየናቸው ዝርያዎች አሉ የሚሉት በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የደንና የግጦሽ ብዝሃ ህይወት ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ አበራ ስዩም ናቸው፡፡
እየተመናመኑ ያሉ ሀገር በቀል እጽዋት የተለዩ አሉ የሚሉት አቶ አበራ የተመናመኑ ስንል ከየአካባቢያቸው የተመናመኑ እና ለመጥፋት የተቃረቡ ዝርያዎች ናቸው፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ለምሳሌ የኰሶ ዛፍ፣ ጥቁር እንጨት እና ቀረሮ ሀገር በቀል ከመሆናቸው በተጨማሪ ለመድኃኒትነት የሚውሉም ናቸው ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ እነዚህን ዝርያዎች ለይቶ ዝርያቸውን ማብዛትና መትከል ወይም መመለስ ያለባቸውን ችግኝ ያሰናዳል ተብሏል፡፡
በተለይ ከባህላዊ የህክምና ስራ ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ የሚውሉት እንደ ኮሶ ያሉ ዕጽዋት እጅግ አስፈላጊ ቢሆኑም ከየአካባቢው የመጥፋት ስጋት ያለባቸው በመሆኑ ትኩረት የሚፈልጉ መሆኑን አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ለመድኃኒትነት የሚውሉና ሀገር በቀል የሆኑ የእጽዋት ዝርያዎችን በመለየት ከኢትዮጵያ የባህል ህክምና አዋቂዎች ማህበር ጋር በመሆን ዝርያዎቹን ማብዛትና በችግኝ ተከላዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ ማድረግ ላይ እየሰራን ነው ብለዋል መሪ ስራ አስፈፃሚው፡፡
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙና ለመድሀኒትነት የሚውሉ ስድስት መቶ ዓይነት የእጽዋት ዓይነት መኖራቸውን የሚናገረው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የሚፈለገው ትኩረት ስላልተሰጣቸው ዝርያቸው እንደጠፋ እና የመጥፋት ስጋት ያሉባቸው መሆኑን በሰራው ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
በአረንጓዴ አሻራም ይሁን ሌሎች በሚደረጉ የችግኝ ተከላዎች ዝርያቸው ከሌላ ሀገራት የሆኑ እጽዋት በብዛት ሲተከሉ ቆይተዋል።
አሁን ግን በተለይ የመጥፋት ስጋት የተጋረጠባቸው ሀገር በቀል እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ እጽዋት አርባ በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments