ሐምሌ 23 2017 - በአዲስ አበባ በጎርፍ ከሚጠቁ አካባቢዎች ንፋስ ስልክ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናት አሳየ፡፡
- sheger1021fm
- Jul 30
- 2 min read
በአዲስ አበባ በ #ጎርፍ ከሚጠቁ አካባቢዎች ንፋስ ስልክ እና አቃቂ_ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናት አሳየ፡፡
የሚነገረው የትንቢያ መረጃ ለ40 በመቶው ነዋሪው ብቻ ነው እየደረሰው ያለው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ላለፉት ዓመታት ሲከወን በመነበረው የአየር ጠባይ የዳሰሳ ጥናት ሁለቱ ክፍለ ከተሞች ተደጋግሞ ጎርፍ የሚያጠቃቸው መሆኑን አሳይቷል፡፡
የአዲስ አበባ ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ እንደሚያሳየው የሰሜኑ የከተማዋ ክፍል ከፍታ ያለው በአንፃሩ የደቡቡ ክፍል ዝቅተኛ ቦታዎች ያሉት ተዳፋታማ መሆኑን ከግምት በማስገባት ነው ጥናቱ የተከወነው፡፡

ከተማዋ የዓመቱን ከፍተኛ ዝናብ በምታገኝባቸው በክረምት ወራት የሚዘንበው ተከታታይነት ያለው ዝናብ ከሰሜን ክፍል በከፍተኛ ፍጥነት ተንደርድሮ ወደ ደቡብ በመምጣት ጎርፍ እንደሚያስከትል ተጠቅሷል፡፡
በተለይ በጥናቱ ትኩረት የተደረገባቸው የንፋስ ስልክና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች በደቡቡ የአዲስ አበባ ክፍል ያሉ፣ ተዳፋት የበዛበት፣ የቤቶቹ አሰራር የቦታውን ተጋላጭነት ያገናዘበ አለመሆኑን እንደተመለከቱ የጥናቱን አስተባባሪና በኢንስቲትዩቱ ዘርፍ ተኮር የሜቴዎሮሎጂ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታረቀኝ አበራ ናቸው፡፡
ጥናቱ የተከወነው ኢንስቲትዮቱ ላለፉት 5 ዓመታት ሲሰራበት በነበረውና በመጪው መስከረም በሚጠናቀቀው ዳራጃ ተብሎ በተሰየመው ፕሮጀክት ሲሆን ከእንግሊዝ መንግስት በተገኘ የ100,000 ፓውንድ የገንዘብ ድጋፍ ነው ተብሏል፡፡
ዋናው ዓላማውም የአዲስ አበባን የአየር ጠባይ ማለትም ሙቀት፣ ቅዝቃዜውን የዝናቡንም መጠን በማጥናት የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎችን በመለየት ለማህበረሰቡም ይሁን ለመንግስት የጥንቃቄ የሚሆን ሳይንሳዊ መረጃዎችን ማደራጀት እንደሆነ የነገሩን የጥናቱ አስተባባሪ አቶ ታረቀኝ፤ በጥናቱ በአቃቂ ቃሊቲ ብቻ 20 የጎርፍ የስጋት ቀጠናዎች ተለይተዋል፤ ከዚህ ውስጥ አደጋው በሚከፋባቸው በ6ቱ ላይ ፕሮጀክቱ እየተተገበረ ነው፡፡ በሙቀት በኩልም በበጋ ወቅት ደቡቡ በከፍተኛ ሙቀት ሲመታ በዚሁ ጊዜ ሰሜኑ እስከ ዜሮ ዲግሪ ሴልሺየስ የደረሰ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ከ641 ቤተሰቦች የተወሰደው ናሙና እንዳሳየው በአካባቢዎቹ ተደጋግሞ ጎርፍ እንደሚከሰት ፤ በአደጋው ወቅት በቤቶቹ ለአደጋ ተጋላጭነት ምክንያት እራሳቸውን ለመከላከል እንደሚቸገሩ፤ ልጆቻቸውን ከአደጋው ለማትረፍ ጠረጴዛና የመሳሰሉት ከፍ ያሉ ነገሮች ላይ ለማድረግ እንደሚገደዱ፣ ነዋሪዎቹ የወር ገቢያቸው ከ3,000 ብር ጀምሮ ያለ ዝቅተኛ መሆኑ ታይቷል፡፡
አደጋው ሲደርስ የሰው ህይወት ላይ ሞትና የንብረት ውድመት ያደርሳል፤ በተለይ በአቃቂ አካባቢ የሚደርሰው የጎርፍ አደጋ በወንዝ ሙላት ምክንያት ስለሚሆን እስከ 1 ወር የሚቆይ መሆኑንም አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል፡፡
በጥናቱ ሌላው የተዳሰሰው የመረጃ ተደራሽነት ነው በዚህም የሸገር ራዲዮን የአየር ትንቢያ መረጃዎች በማህበረሰቡ ተመራጭ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በከዚህም በተጨማሪ በቴሌቪዥን፣ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በኢንስቲትዩቱ ዌብሳይት የትንቢያ መረጃዎቹ ይደርሳቸዋል፡፡
ይሁንና አጠቃላይ ከተማዋ የትንቢያ መረጃ በትክክል እየደረሰ ያለው ከ40 በመቶው ነዋሪ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል ያሉን ሀላፊው በምክረ ሃሳብነት የተጠቀሱትንም ነግረውናል፡፡
በተለይ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑት በእነዚህ አካባቢዎች ተገቢው የጥንቃቄ ስራ እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል የትንቢያ መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ወደ ማህበረሰቡ እንዲደርሱ በሚዲያዎች በተከታታይ ቢነገር፤ በተቻለ መጠን በእጅ ስልኮች እንዲደርሳቸው ቢደረግ ተብሏል፡፡
ጥናቱ የተከወነበት የዳራጃ ፕሮጀክት ከሁለት ወራት በኋላ ቢጠናቀቅም መሰል የጥናትና ምርምር ስራዎች የጎርፍ ተጋላጭ ናቸው ብሎ በመረጣቸው በጅግጅጋና በድሬዳዋ ለመቀጠል ተጨማሪ በጀት ማግኘቱን ከኢንስቲትዩቱ ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/23523/
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments