ሐምሌ 23 2017 -መርካቶ ሸማ ተራ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ
- sheger1021fm
- Jul 30
- 1 min read
ጥቅምት 11 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ #መርካቶ ሸማ ተራ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ በርካታ ውድመት ማስከተሉ ይታወሳል።
በሰው እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል።
በወቅቱ በስፋት ሲነገሩ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የከተማዋ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለማጥፋት #ገንዘብ ሲደራደሩ፤ ሲቀበሉ ነበር የሚለው ይገኝበታል።
ይሄን ተከትሎም ፖሊስ ለወራት ጉዳዩን ሲከታተል እና ሲመረምረው ቆይቷል።
ፖሊስ በምርመራውም ሲነገር የነበረው ሰራተኞቹ በወቅቱ ገንዘብ ተደራድረዋል፤ ተቀብለዋል የተባለው መረጃ ሃሰት መሆኑን አረጋግጧል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነግሮናል።

የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ጥቅምት ወር ላይ በአዲስ አበባ መርካቶ ሸማ ተራ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ፤ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ከማጥፋት ይልቅ 4 ሚሊዮን ብር እንዲሰጣቸው ተደራድረዋል የሚል ወሬ በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ነበር ብለዋል።
ሆኖም ፖሊስ ባደረገው ጥልቅ የማጣራት ስራ የተባለው ነገር ሀሰት መሆኑን ፖሊስ ማረጋገጫ ሰጥቶናል ይላሉ።
በሸማ ተራ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ከማጥፋት ይልቅ በገንዘብ ሲደራደሩ፣ ሲቀበሉ ነበር ብለው ባሰራጩ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ኮሚሽኑ ክስ መስርቻለሁ ብሎ ነበር።
ይህን በተመለከተም ጉዳዩን ፖሊስ እንደያዘው ሰምተናል።
በዚህም በሀሰት የተቋሙን ስም አጥፍተዋል የተባሉ ስምንት ማህበራዊ ሚዲያ ሰዎች ላይ ክስ እንደተመሰረተባቸው አቶ ንጋቱ ነግረውናል።
የኮሚሽኑ ስራ ህይወትም ጭምር መስዋዕትነት የሚደረግበት ነው ያሉት አቶ ንጋቱ በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚሰራጨው ሳይሆን የተቋሙ ስራ በራሱ ግልጽ የሆነ በመሆኑ ለሙስና የሚመች አይነት አይደለም ብለዋል።
ፍቅሩ አምባቸው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments