ሐምሌ 16 2017 - የሚሊኒየም አዳራሽ አሁን ካለበት ደረጃው ተሻሽሎ እንደ አዲስ ሊገነባ ነው ተባለ።
- sheger1021fm
- Jul 23
- 1 min read
በኢትዮዽያ ግዙፉ አዳራሽ ባለፈው ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ምሽት ያጋጠመው የእሳት አደጋ መነሻ ምክንያትም በሚመለከተው አካል እየተጣራ ነው፤ ጊዜው ሲደርስ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳለው ከመጪው ዓመት ታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ #ሚሊኒየም_አዳራሽ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩና አሁን ከሚሰጠው አገልግሎት በላቀ ደረጃ እንዲሰጥ ታስቦ እንደ አዲስ ግንባታ ይደረግለታል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኘው አዲስ ፓርክ እና ማኔጅመንት በተለምዶ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተባለ የሚጠራው በኢትዮዽያ ውስጥ ከሚገኙ ግዙፍ አዳራሾች መካከል ከቀዳሚዎቹ መሆኑ ይታወቃል።
ሚሊኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን ታሳቢ አድርጎ በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ የተለያዩ አገልግሎቶችን ባለፉት ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል።

እስከ 25,000 ሰዎችን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ አቅም ያለው የሚሊኒየም አዳራሽ 20,000 ስኩየር ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ መሆኑን #ሚድሮክ_ኢንቨስትመንት_ግሩፕ ተናግሯል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ ዝግጅቶችን ሲያተናግድ የቆየው አዳራሹ በኢትዮዽያ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ 19 ችግር ወቅትም ሙሉ በሙሉ ለህክምና አገልግሎት መስጫነት መዋሉም ይታወሳል።
የሚሊኒየም አዳራሽ በለፈው ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ምሽት አገልግሎት እየሰጠ በነበረበት ወቅት የእሳት አደጋ አጋጥሞት የነበረ ሲሆን የስራ ሀላፊዎቹ እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የተጎዳው ተስተካክሎ ወደ አገልግሎት ተመልሷል።
የችግሩ ምክንያትም እየተጣራ ነው፣ ጊዜው ሲደርስም ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








