ሐምሌ 15 2017 - የህዳሴ ግድብ ግንባታ ቢጠናቀቅም፤ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራውን እንደሚቀጥል የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅ/ቤቱ ተናገረ፡፡
- sheger1021fm
- Jul 22
- 1 min read
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቢጠናቀቅም፤ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራውን እንደሚቀጥል የግድቡ ማስተባበሪያ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተናገረ፡፡
ከዚህ በኋላ ህዝቡ የሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ለኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር ዝርጋታ፣ ለተፋሰስና ሌሎች ስራዎች ሊውል እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡
የመገናኛ ብዙሃንን ጠርቶ በተጠናቀቀው የ2017ዓ.ም በግድቡ ገቢ አሰባሰብና ሌላውንም ስራ ያብራራው ጽህፈት ቤቱ በዓመቱ በተለያየ መንገድ ከህዝቡ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግሯል፡፡
ህዝቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተጠናቀቀ ድጋፉ እንዲቀጥል ለምን ተፈለገ? ተብለው የተጠየቁት መግለጫውን የሰጡት የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር)፤ ግንባታው ቢጠናቀቅም ሌሎች ስራዎች ስለሚቀጥሉ ነው የህዝቡ ድጋፍ ቀጥል የምንለው በማለት 3 ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው አባባል ግድቡ ረጅም እድሜ እንዲኖረው በደለል መሞላት የለበትም ይህ እንዳይሆን ለሚሰራው የተፋሰስ ስራ ገንዘብ ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም የተመረተውን የኤሌክትሪክ ሃይል በየቤቱ ለማድረስ የሚሰራው ሰፊ የማሰራጫ መስመር ዝርጋታ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ነው ድጋፉ መቀጠል ያለበት ብለዋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ በአዋጅ ስራውን ያቁም እስከሚባል ድረስ የማስተባበር ስራውን ይቀጥላል የተባለ ሲሆን በተጨማሪም አረጋዊ(ዶ/ር) በአንድ ግድብ አንቆምም ተጨማሪ የመስኖም ይሁን ሌላውን ግድብ ለመስራት የህዝቡ ድጋፍ ያስፈልጋል ሲሉ ገቢ ማሰባሰቡ ይቀጥላል ያሉበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡
የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች ቀጥለዋል ያለው ፅህፈት ቤቱ በ2017 ዓመት ብቻ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በ14 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ከህዝቡ መሰብሰቡን ሲናገር ሰምተናል።
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








