ሐምሌ 15 2017 - ''1 ዓመት የሞላው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ፤ እስካሁን በመሰረታዊ መልኩ የዋጋ ግሽበቱን አላስተካከለውም'' የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ
- sheger1021fm
- Jul 22
- 2 min read
ኢትዮዽያ የወሰደችው 1 ዓመት የሞላው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ፤ እስካሁን ድረስ በመሰረታዊ መልኩ የዋጋ ግሽበቱን አላስተካከለውም ተባለ።
ይህን ያሉት የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ናቸው።
እሳቸው አያይዘውም በቅርቡ በኢትዮዽያ #የዋጋ_ንረት ወደ ነጠላ አሀዝ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።
ስር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ ችግር ለማስተካከል እና ያልተረጋጋ የፋይናንስ ስርአት ለማሻሻል የተወሰደው ማሻሻያ ውጤት ምንድነው? በማለትም የኢትዮዽያ የፋይናንስ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።
ይህን ጉባኤ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገንዘብ እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አዘጋጅተዋል።

ባለፈው ዓመት ኢትዮዽያ የወሰደችው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲና የማክሮ ኢኮኖሚና መዋቅራዊ ማሻሻያ ምን ውጤት አመጣ የሚለው ነጥብ ተነስቷል።
የገንዘብ ፖሊሲ በምን እንደሚመራ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን አወሳሰን እና ገበያ እንዲሁም የፊስካል ፖሊሲ እና አጠቃላይ የፋይናንስ ጤና በተመለከተ የፋይናንስ ጉባኤው ውጤቱን ገምግሟል።
ኢትዮዽያ በወሰደችው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ምን ውጤት ተገኘ በሚለው ጉዳይ ፖሊሲ አውጭ እና አስፈፃሚዎች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ቅድሚያ ጥያቄ የቀረበላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ምኒስትር አህመድ ሽዴ፤ ይህ ጥብቅ የፖሊሲ እርምጃ ሲወሰድ በህብረተሰቡ ላይ የሚኖረው ጫና ይጠበቃል፤ ስለዚህ ከለውጡ ጋር በተገናኘ በህዝቡ ላይ ጫና ለመቀነስ ምን ምን ሰራ፣ ተሰሩ ? ተብለው ተጠይቀዋል።

ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፤ የግሉ ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ ተረጋግቶ እንዲኖር የተደረጉ ማሻሻያዎች አሉ ብለዋል።
የግል ባንኮች ከአስገዳጅ ቦንድ ተላቀው ለግሉ ዘርፍ ብድር እንዲለቁ ተደርገዋል ሲሉ መልሰዋል።
የግሉ ዘርፍ በማሳደግ ረገድም ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ለውጥ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ሪፎርሙ በዝቅተኛ ዜጋ ላይ የሚኖረው ዋጋ ልዩነት ጫና እንዳያመጣ ከፍተኛ የሆነ የደመወዝ ጭማሪ ተደርጓል ብለዋል።
ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ የደመወዝ ድጎማ በሌሎችም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ድጎማ አድርጓል ብለዋል።
በጠቅላላው ለውጡ የዋጋ ግሽበት ከመቆጣጠር መዓዘን ጥሩ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
ሌላው ይህ አንድ ዓመት የሞላው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ምን ለውጥ አመጣ ተብለው የተጠየቁት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ጥያቄውን በሶስት ከፍለውታል።

ለውጡ በመጀመርያ እስካሁን ድረስ በመሰረታዊ መልኩ ያልተፈታውን የዋጋ ግሽበት ለማስተካከል፤ ስር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ ችግር ለማስተካከል እና ያልተረጋጋ የፋይናንስ ስርአት ለማሻሻል ሲሉ አስረድተዋል።
በዚህም የገንዘብ ፖሊሲን ዘመናዊ ለማድረግ፤ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ በመቀየር የዋጋ ንረት ችግር ከበፊቱ በግማሽ ተፈቷል ብለዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ፤ ዘመናዊ ከማድረግ መዓዘን ባንኮች ሲፈልጉ ከብሔራዊ ባንክ እንዲበደሩ በማስቻል በኩል ጥሩ ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።
የኢትዮዽያ የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር እና አሰራር በመቀየር፤ የተሻለ እና ደጋፊ መመሪያ በማምጣት ለውጥ አምጥተናል ብለዋል።
በአጠቃላይ ይህ ሪፎርም ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት እና ተጠባባቂ ክምችት የውጪ ምንዛሪ የጨመረበት ነው ሲሉ መልሰዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ግብርና እንዲሻሻል የተቀረፀው ፖሊሲና ለውጦች ችግሮችን ለመፍታት ምን ተሰራ ተብለው የተጠየቁት የግብርና ሚኒስቴር ግርማ አመንቴ፤ በግብርናው ሴክተር ለውጥ መጥቷል፤ በበሬ ከማረስ ለመላቀቅ በማሰብ የተደረጉ ለውጦች አሉ ብለዋል።
ባለሀብቶች መሬት ሳይሻሙ ከአርሶአደሮች ጋር በሽርክና በመሆን በግብርና መአዘን ሰፋፊ እርሻ በማሳተፍ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት ግብርናው በአየር ንብረት ለውጥ እንዳይደናበር በሁሉም ወቅት ለማምረት መንገድ ተይዟል ብለዋል።
ሌላኛው ጥያቄ የቀረበላቸው የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ የሀይል ዘርፍ ሪፎርም ምን ለውጥ አመጣ?፤ ከዋጋ ከቁጥጥር እና ከማከፋፈል መዓዘንስ ተብለው ተጠይቀዋል።
እርሳቸውም ባለፈው ዓመታት ሀይል የማምረት አቅም አድጓል ብለዋል።
በየዓመቱ የነፍስ ወከፍ የሀይል ፍጆታ ጨምሯል፣ ዜጎች በተቻለ መጠን የሚችሉትን ታሪፍ መክፈል እንዲችሉ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments