top of page

ሐምሌ 15 2017 - ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው መጋቢት ወር ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሀገራቸው ምርቶቻቸውን በሚልኩ 100 ሀገራት ላይ የጣሉት ታሪፍ

  • sheger1021fm
  • Jul 22
  • 2 min read

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው መጋቢት ወር ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሀገራቸው ምርቶቻቸውን በሚልኩ 100 ሀገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።


ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ የጣሉት የ10 በመቶ ታሪፍ ነው።


በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው የ10 በመቶ ታሪፍ በሁሉም ሀገራት ላይ የተጣለው የመነሻ ታሪፍ ( #Baseline_Tariff ) እንደሆነ ተመልክቷል።


ኢትዮጵያ ቀደም ብላ አሜሪካ ከሰሃራ በስተደቡብ ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሰጠችው የታሪፍ እና ኮታ ነጻ ዕድል ወይም አጎዋ መታገዷ ይታወሳል።


ከአጎዋ ዕገዳ በኋላ የተሰማው ይህ የታሪፍ ውሳኔ በአንድ በኩል ወደ አሜሪካ የሚገቡ የኢትዮጵያ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ከፍ እንዲል በማድረግ ፍላጎቱን ሊቀንሰው ይችላል ሲባል ቆይቷል።


በሌላ በኩል ሌሎች አገራት ላይ ከተጣለው ከፍ ያለ ታሪፍ አንጻር የኢትዮጵያው አስር በመቶ ብቻ መሆኑ ምርቶቻችን የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ ሊረዳ ይችላል የሚል ትንበያም አሰጥቷል፣ ከፍ ያለ ታሪፍ በምርቶቻቸው ላይ የተጣለባቸው ሀገራት የመሸጫ ዋጋቸውን ማሳደጋቸው አይቀርም፣ አነስተኛ ታሪፍ በምርቶቿ ላይ የተጣለባት ኢትዮጵያ የመሸጫ ዋጋዋን በእነሱ ልክ ልታድርግ ስለ ማትችል የተሻለ ገበያ ይኖራታል ነው የሃሳቡ መነሻ።


በንግድ ዙሪያ ምርምር የሚያደርጉ አራት የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎችን ያካተተ አንድ ቡድን የተጣለው ታሪፍ የእስከ አሁን እንድምታን የተመለከተ ጥናት አካሂዶ ውጤቱን አሳውቋል።


በዚህም ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው ምርቶች የተወሰኑት በታሪፉ ምክንያት ተጽዕኖ እንዳገኛቸው፤ ሌሎች የተወሰኑት ጥሩ ገበያ እንደተከፈተላቸው፤ የተቀሩት ደግሞ ለውጥ ሳያሳዩ እንደቀጠሉ አመልክቷል።


በታሪፉ ምክንያት ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ ገበያ በአሜሪካ አግኝተዋል ከተባሉት መካከል የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች ተጠቅሰዋል።


ወደ አሜሪካ የሚላኩ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች በአንድ በመቶ መጨመራቸው የተነገረ ሲሆን የቆዳ ውጤቶች ደግሞ በ2 በመቶ ጨምረዋል ተብሏል፤ በተቃራኒው የቬትናም ፤ ቻይና ፤ ህንድ እና ባንግላዴሽ ምርቶች መቀነሳቸውን የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት ታደለ ፈረደ(ዶ/ር) ነግረውናል።


ታሪፉን ተከትሎ መቀነስ ታይቶባቸዋል የተባሉት ደግሞ የቅባት እህሎች ናቸው።


የትራምፕን የአስር በመቶ ታሪፍ ተከትሎ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው የቅባት እህሎች በ 0 ነጥብ 1 በመቶ መቀነሳቸውን ጥናቱ አሳይቷል።


በርግጥ ከፍተኛ የቅባት እህል ወደ አሜሪካ በሚልኩት አርጀንቲና እና ብራዚል ላይም ቅናሽ ይኖራል የሚል ሰፊ ግምት እንዳለ ተጠቅሷል።


ቡና እና አበባ ደግሞ በታሪፉ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሳያርፍባቸው ቀጥለዋል የተባሉ ምርቶች ናቸው።


የአበባ ምርት በመግዛት አሜሪካ ከአለም ቀዳሚዋ አገር ስትሆን ከዚህ ገበያ የኢትዮጵያ ድርሻ 0.2 በመቶ እንደሆነ ተጠቅሷል።


ትራምፕ የጣሉት ታሪፍ በአበባ ምርት በኩል ለኢትዮጵያም ሆነ ለተፎኳካሪዎቿ ያመጣውም ሆነ ያሳጣው ነገር እንደሌለ ዶክተር ታደለ ነግረውናል።ቡናም በዚሁ መንገድ የሚታይ ነው ብለዋል።


የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካ የተጣለውን ታሪፍ በበጎ መልኩ እንደሚያየው በዚያው ሰሞን መናገሩ ይታወሳል።


የተጣለው የአስር በመቶ ታሪፍ የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ አሜሪካ ገበያ ሲገቡ ተወዳዳሪነታቸውን ያሳድጋል ነው ያለው።


ውሳኔው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እና የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ለማሳደግም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ጠቅሷል።


ዶክተር ታደለ ግን ታሪፉ አዎንታዊም ፤ አሉታዊም ጎን ስላለው በደፈናው ተቀብለንዋል ማለቱ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው 92 በመቶውን የሚሸፍኑት አስር የምርት አይነቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።


እነዚህ ምርቶች በዋናነት የሚላኩት ወደ እስያ እና አውሮፓ ገበያዎች እንደሆነም ጥናቱ ያመለክታል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…….


( ተያያዥ ዘገባን ለማንበቡ… https://shorturl.at/ZKOH6 )


ንጋቱ ረጋሳ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page