ሐምሌ 12 2017 - ሳንቲምፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽንስ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ የሆነውን የፖስ ማሽኖችን በሀገር ቤት መገጣጠም ጀመርኩ አለ።
- sheger1021fm
- Jul 19
- 2 min read
Updated: Jul 22
የዚህ ማብሰሪያ ስነ ስርዓትም በዛሬው ዕለት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
በስነስርዓቱ ላይም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) እንዲሁም የተለያዩ የባንክ ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል።
የክፍያ ስርዓት አቀላጣፊ የሆነው ሳንቲምፔይ ባቋቋመው #የፖስ_ማሽን መገጣጠሚያ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ሲሰራ በቀን 3,000 የፖስ ማሽኖች መገጣጠም እንደሚችል ተነግሯል።
የፖስ ማሽኖቹ በ5 ቋንቋዎች እንደሚሰሩ ተነግሯል።
የፖስ ማሽኖቹ በሀገር ቤት መመረት መጀመር፤ ሀገር ማሽኖቹን ከውጪ ለመግዛት የምታወጣውን ዶላር ያስቀርላታል ተብሎ ታምኖበታል።
ከዚህ በተጨማሪም የፖስ ማሽኖችን ዋጋ እስከ አስር በመቶ እንዲቀንስ ያስችለዋል ሲባል ሰምተናል።
የፖስ ማሽኖቹን የሚገጣጥሟቸው የሀገር ልጆች እና ሶፍትዌሮቹም የበለፀጉት በኢትዮጵያን መሆኑን የሳንቲምፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ትንሳኤ ደሳለኝ ተናግረዋል።
ሳንቲምፔይ የፖስ ማሽኖቹን መገጣጠም ከጀመረ 3 ወር እንደሆነውና ለባንኮች እና ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ማቅረብ መጀመሩን አስረድቷል።
ማሽኖቹን ወደ አፍሪካ ሀገራት ለማቅረብ ዝግጅት መጀመሩንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል።
የፖስ ማሽኖች በሀገር ውስጥ መገጣጠም መጀመር በሀገሪቱ በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ የግብይት ስርዓትን ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያሻሽለው ተጠቅሷል።

በመላው ኢትዮጵያ ያሉት የፖስ ማሽኖች ብዛት 20,000 የማይበልጡ፣ ከዚህ ወስጥም በብልሽት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ አንዳሉ ሲነገር ሰምተናል።
አነስተኛ የፖስ ቁጥር ሊኖር የቻለውም ማሽኖቹን እና ሶፍትዌሩን ከወጭ ሀገር እንደልብ ለመግዛት ዋጋቸው ወድ መሆኑ በዋና ምክንያትነት የተጠቀሰ ሲሆን ሳንቲምፔይ መገጣጠም መጀመሩ ችግሩን እንደሚቀርፈው ተነግሯል።
ከፖስ መገጣጠሚያ ፋብሪካው ጎን ለጎን የጥገና አገልግሎት የጥገና ማዕከልም ተቋቋሟል ተብሏል።
ይህም ከዚህ ቀደም ፖስ ማሽኖች ሲበላሹ ለጥገና ወደ ውጭ ሃገር ይላክ የነበረውን ሂደት ያስቀራል ሲባል ሰምተናል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ፖስ ማሽኖችን ከአውሮፓና ከቻይና በመግዛት ለሃርድ ዌር እና ሶፍትዌር ታወጣ የነበረውን የውጪ ምንዛሪ ከማዳን አኳያ ይህ የፖስ መገጣጠምያ ማዕከል ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል ተብሎ ተስፉ ተጥሎበታል።
በሌላ በኩል ሳንቲምፔይ በዩናትድ አረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ሳኑ ፔይ ከተባለው ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ኦፕንዌይ የተባለ ስዊችን ተግባራዊ በማድረግ ለባንኮች እና ለተለያዩ የፋይናንሻል ተቋማት ዘመናዊ የክፍያ ስርአትን ማቅረብ መጀመሩን ተናግሯል።
ይህ ስዊች በተለይም በኢትዮጵያ ገና ያልተጀመረውን የክሬዲት ካርድ፣ ቨርቹዋል ካርድ እና ሌሎች ተጨማሪ ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን ይህም ግብይቶችን ዲጅታል ለማድረግ ያግዛል ተብሏል።
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








