ሐምሌ 11 2017 - ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞ ተማሪዎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ተቋማዊ ለማድረግ የሚስችለውን ደንብ አሰናድቶ ማጠናቀቁን ተናገረ
- sheger1021fm
- Jul 18
- 1 min read
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞ ተማሪዎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ተቋማዊ ለማድረግ የሚስችለውን ደንብ አሰናድቶ ማጠናቀቁን ተናገረ፡፡
ጎንደር ዩኒቭርሲቲ ከሰኔ 30 ቀን 1949 ዓ.ም ጀምሮ በ66 ጊዜ ከ107,800 በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ ደረጃዎች አስተምሮ ማስመረቁን ተናግሯል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን(ዶ/ር) ትናንት ጉዳዩን አስመልክተው በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ሃምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም የአልሙናይ ቀን እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

በዚህ ቀን የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዳግም የሚገናኙበት፣ ስለቀድሞ ተቋማቸው የሚመካከሩበት ዩኒቨርሲቲያቸውን በሃሳብ፣ በእውቀት፣ በቁስ እና በገንዘብ እንዴት ማገዝ እና መርዳት እንዳለባቸው ሃሳብ የሚለዋወጡበት ይሆናል ተብሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከቀድሞ ተመራቂ ተማሪዎች ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ተቋማዊ እንዲሆን ስርዓት ሲዘረጋ መቆየቱንና አሁን መጠናቀቁን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡
የተመራቂ ተማሪዎች መመዝገቢያ ስርዓት ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተደራጅቶ፣ ምሩቃንም መመዝገብ ጀምረዋል ያሉት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ያልተመዘገቡም በዚህ ስርዓት እንዲመዘገቡ ጠይቀዋል፡፡
መመዝገብያ ስረዓቱ የተመራቂዎችን መረጃ ከተማሪነት አሁን እስካሉበት ደረጃ ድረስ የሚይዝ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ዛሬ ይፋ ይደረጋል ተባሏል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው በዛሬው እለት የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ወይም ምሩቃን ማህበር በይፋ ይመሰረታል ብለዋል፡፡
ለዚህም የማህበሩ የመተዳደርያ ደንብ እና የመለያ ምልክት (logo) ለህዝብ ግልጽ ይደረጋል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከዚህ ቀደም ተመራቂዎች ሲደርጉት የነበረውን የተበታተነ ድጋፍ መስመር ያስይዛል፤ ዩኒቨርሲቲው ከቀድሞ ተማሪዎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ተቋማዊ ለማድረግ ይረዳዋል ተብሏል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሻለ ስራ የሰሩ የቀደሞ ተመራቂ ተማሪዎችን በህዝብ ጥቆማ በ12 መደብ ሊሸልም መሆኑንም ተናገሯል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው በነገው እለት በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 2,500 ተማሪዎች እንደሚስመርቅ አስረድተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments