ሐምሌ 11 2017 - ለቤት ሰራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲቀመጥ ተጠየቀ።
- sheger1021fm
- Jul 18
- 2 min read
የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን በመከውን ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን የሚያቀርበው ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ( #FSS ) የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የሰራተኞቹን ጥቅም ያስከብራል ያለውን ሞዴል ህግ አዘጋጅቷል።
ተቋሙ ህጉን አስመልክቶ ከባለድርሻዎች ጋር በመከረበት ወቅት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ የቤት ሰራተኞች እንደ ማንኛውም ሰራተኛ ቢቆጠሩም የሚተዳደሩበት የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ለመብት ጥሰት ይዳረጋሉ ብሏል።
አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስችል ዝርዝር የህግ ማዕቀፍ ሳይወጣ ከዛሬ ነገ ይወጣል በሚል 32 ዓመታት ተቆጥረዋል የሚለው ተቋሙ ህጉን ለማውጣት መነሻ እንዲሆን የFSS የህግ ሞዴል በሚል ያዘጋጀውን ምክረ ሃሳብ ይፋ አድርጓል።
በዚህም በምክረ ሃሳቡ ከሰፈሩት መካከል አንዱ እስካሁን ለቤት ሰራተኞች የሚከፈለውን ደመወዝ የሚዳኝ ህግ ባለመኖሩ ይወጣል ተብሎ በሚጠበቀው የህግ ማዕቀፍ ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል መቀመጥ አለበት የሚል መሆኑን የነገሩን በዝግጅቱ ተሳታፊ የነበሩት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሙሴ መዝገበ ናቸው።
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በሃገሪቱ ባልተወሰነበት ሁኔታ ይህ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል ስንል የጠየቅናቸው ተመራማሪው፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ባይኖርም እንደ ቤት ሰራተኞች ላሉ ትንንሽ ተከፋዮች በየዘርፉ ከፋፍሎ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዘርፉን አስመልክቶ በሚወጣው ህግ ቢካተት የተባለው ሌላው የቤት ሰራተኞች የስራ ሰዓት ገደብ ነው።
በአዋጁ ለመደበኛ ሰራተኞች የተቀመጠው የ8 ሰዓት የስራ ሰዓት ለቤት ሰራተኞችም ተግባራዊ መደረግ አለበት ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የቤት ሰራተኞች እርግዝና ሲገጥማቸው ከሳራቸው ስለሚባረሩ ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚዳረጉበት ጊዜ አለ የሚሉት ፕሮፌሰር ሙሴ ሰራተኞቹን ከእነዚህና ከሌሎችም ችግሮች ለመጠበቅ ደመወዛቸው ሳይቋረጥ የወሊድ ፍቃድ ሊሰጣቸው ይገባል የሚለውም መካተት እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ይሁንና ሳይሰሩ የሚያገኙትን ደመወዝ መንግስት በማህበራዊ ዋስትና አካቶ ሊከፍላቸው ይገባል ይህ አሰራር የጎረቤት ሃገራት ሳይቀሩ የሚጠቀሙበት ነው ይላሉ።
በኢትዮጵያ እስካሁን የቤት ሰራተኞችን መብት የሚያስጠብቅ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በቤት ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው የጉልበት ብዝበዛና የቤት ውስጥ ጥቃቶች ቀጥለዋል ተብሏል።
ይህንን ለማስቀረትና ዘርፉንም ወደ መደበኛ የስራ ዘርፍ ለመቀየር ያግዛል የተባለው የህግ ማዕቀፍ ከዛሬ ነገ ይወጣል እየተባለ እስካሁን መውጣት ያልቻለው ህግ አውጪዎቹ በራሳቸው የቤት ውስጥ ሰራተኞች ያላቸው በመሆኑ የሰራተኞቹን ጥቅም የሚያስከብር ህግ ሲወጣ የአሰሪዎቹ ጥቅም ይነካል ከሚል ፍራቻ እንደሆነ በውይይቱ ተነስቷል።
አዋጁን የሚያስፈፅመው የህግ ማዕቀፍ ሲወጣ እንዲህ አይነት ስጋቶች እንዳይኖሩ በተቻለ መጠን የቤት ሰራተኞቹን ሃሳብ ማካተት እንደሚገባ ከጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል የሆኑት ዶክተር ሰላም ኢሳያስ አሳስበዋል።
ይህ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የቀረበው ምክረ ሃሳብ ተከታታይ ውይይቶች ተደርጎበት ለፖሊሲ አውጪዎች ይቀርባል መባሉን ሰምተናል።
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments