ሐምሌ 1 2017 - ከህዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ አይደሉም ሲሉ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ
- sheger1021fm
- 4 hours ago
- 3 min read
ምክር ቤቱ በበኩሉ መቶ በመቶ እና በሚፈለገው ልክ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ማለት ባይቻልም ትልልቅ ለውጦች መጥተዋል ብሏል፡፡
የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት የሚሰጧቸው ጥቅማ ጥቅሞችም እንዲሻሻሉ ጠይቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ በበኩሉ በሚፈለገው ልክ ባይሆንም ጥያቄዎች እየተመለሱ ናቸው ብሏል፡፡
የምክር ቤት አባላት ይህን የጠየቁት የምክር ቤቱ የ2017 ዓ.ም የስራ ክንውን ሪፖርት በቀረበበት ወቅት፡፡
የሪፖርቱን ማብቃት ተከትሎ ሀሳባቸውን የሰጡ አንድ የምክርቤት አባል ከህዝብ ጋር በነበረን ውይይት ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አንድም አልተመለሱም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለምሳሌ ተጀምረው የቆሙ የመንገድን ፕሮጀክቶች በሁሉም ክልሎች አሉ ያሉት የምክር ቤት አባሉ 4 ዓመታት ሙሉ ለውክልና ስራ በሄድንበት ወቅት የሚነሳ ጥያቄ ስለሆነ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ጣልቃ ገብተው ይህን ጉዳይ ቢመለከቱ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ በማከልም የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ጥቅማጥቅም ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች አሉ እነሱስ የት ደረሱ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላው ሃሳባቸውን የሰጡት እና ጥያቄ ያቀረቡት የምክር ቤት አባል መብራቱ ማሴቦ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የምክር ቤቱ የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎች ምን ያክል ውጤታማ እንደሆኑ ምክር ቤቱ የራሱ የምርምር ተቋም ስላለው ቢያጠናው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሚዲያ እኔ ስመለከት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ደግሞ ቋሚ ኮሚቴወዎችን ማሞጋገስ ይበዛል ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ መሞጋገሱ ቢቀር እና በልኩ ቢሆን የተሸለ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
የወጡ ህጎች ምን ያህል ተፈጻሚ ናቸው ሲሉ የጠየቁት መብራቱ(ዶ/ር) በተለይ እኔ የማስታውሰው ነዳጅ ላይ ያወጣነውን ህግ ወደ ታች ሲወረድ በፍጹም ተግባራዊ አልሆነም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ለምሳሌ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብትሄዱ፤ አንደኛ ማድያዎች ነዳጅ የላቸውም፡፡ የመንግስት ተቋማት ራሱ ነዳጅ በህገ ወጥ ነው የሚገዙት ያሉት የምክር ቤት አባሉ አንዳንዴ የምናወጣቸው ህጎች ለምን እንደወጡ በሚዲያ ማስረዳት ቢቻል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላው ሃሳቤን መስጠት የምፈልግበት ጉዳይ ከሰላም እና ጸጥታ ጋር ነው ያሉት አቶ መብራቱ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሶስቱ ዞኖች ሁለቱ ተመልሰው ውደ ችግር እየገቡ ስለሆነ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ቢመለከተው፣ ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ያሉ አልሚዎችም አካባቢውን ለቀው እየወጡ ስለሆነ ብለዋል፡፡
የምክር ቤት አባላትም ፕሮቶኮል በተመለከተ ምክርቤቱ ማስተካከያ እንዲያደርግ የጠየቁት መብራቱ (ዶ/ር) የምክር ቤት ኣባላት ክብር እንዲጠበቅ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ የምክርቤት አባላት የሚከፈላቸው ማትግያ በጣም ትንሽ ነው ያሉት የምክር ቤት አባሉ ለምሳሌ ለህዝብ ውክልና ወደ ክልል ስሄድ የተሰጠኝ ክፍያ መንገድ ላይ ነው ያለቀው ወደፊት ይህን ታሳቢ ያደረገ ክፍያ ቢሰጥ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ከህዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ለምሳሌ ወደ አማራ ክልል ለውክልና ስራ በሄድንበት ወቅት መንገድ ላይ ብቻ 119 ጥያቄ ቀርቧል፣ ከዚህ ጥያቄ ውስጥ ምን ያህሉ ተመልሷል ቢባል በጣም አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ በላፉት አራት ዓመታት የተመለሱ ጥያቄዎች ብለው ሪፖርት ማቅረባቸውን ያስተወሱት የምክርቤት አባሉ ከቀረበው ውስጥ ምን ያክሉ ተመልሷል ብዬ ሳስብ አይደለም ጥያቄ ሊመለስ ቀርቶ የተጀመረውን እንኳን ማስቀጠል አልተቻለም፣ ለመሳያም በአማራ ክልል ብቻ የ6.5 ቢሊዮን ብር ካሳ ጥያቄ ምላሽ አላገኝም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ጉዳዮች በቀጣይ ቢስተካከሉ ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ቢነሱም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዳሳነች አካባቢ መወከላቸውን ያስተውሱት የምክር ቤት አባሏ የአንድ የኢትዮጵያ የምክር ቤት ተወካይ እና የኬንያ ተወካይ የሚያገኙት ክፍያ ሲተያያ እንደማይገናኝ ተናግረው ጥያቴያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ተማጽነዋል፡፡

ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የምክርቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በህዝብ ውክልና ስራ ላይ ለውጥ አለ ወይ? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ ይህ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ብለዋል ምክንያቱም ትልልቅ ለውጦች ያየንበት ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና መቶ በመቶ እና በሚፈለገው ልክ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ማለት እንደማይቻል ምክትል አፈ ጉባዔዋ ተናግረው በታች እርከን ላይ ያሉ ጥያቄዎችም ጭምር ግን የተመለሱበት ዓመት ነበር ብለዋል፡፡
ከክፍያ እና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ እየተነሱ ስለሆነ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
መሞጋገስ በዝቷል በሚል ለቀረበው ትችትም ወ/ሮ ሎሚ በምላሻቸው ሃሳቡን እንደሚቀበሉ ተናግረው በጥቅል አያስፈልግም ሳይሆን በአግባብ ቢሆን መልካም ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments