ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት በቀሩትና በመንግስት ወጥቶ ላለፉት 2 ዓመት ሲተገበር ከቆየው የኪራይ ውል ወጪ በአዲስ አበባ በቤቶች ላይ ከፍትኛ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑ ተነገረ፡፡
- 5 hours ago
- 2 min read
ግንቦት 7/2018
ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት በቀሩትና በመንግስት ወጥቶ ላለፉት 2 ዓመት ሲተገበር ከቆየው የኪራይ ውል ወጪ በአዲስ አበባ በቤቶች ላይ ከፍትኛ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑ ተነገረ፡፡
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት በህብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫናና በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ በየቀኑ ሰማይ እየነካ የሄደው የዋጋ ንረት የሸማቹን የመግዛት አቅም በእጅጉ አዳክሞታል፤ ለዚህም መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ተናግሯል።
በተለይም ባለፉት 2 ዓመታት የነበሩ የኪራይ ውሎች መጠናቀቅን ተከትሎ ከ50 እስከ 100 በመቶ የሚደርስ የኪራይ ጭማሪ በተከራዮች እየተደረገ ነው ይህንንም አረጋግጫለሁ ብሏል ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፡፡
የሸማቹ የመግዛት አቅም መዳከም ደግሞ አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን አቀዝቅዞታል፤ በተጨማሪም በነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭት፣ እጥረትና የዋጋ ጭማሪ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል ሲል ተናግሯል፡፡
ድርጅቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ጥናት ለኪራይ ንረቱ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁኔታዎች መታዘቡንና ጭማሪም መደረጉን ተመልክቷል ሲሉ የድርጅቱ መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ቁምላቸው አበበ ነግረውናል፡፡
አብዛኛው ተከራይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው በመሆኑ ካለው የኑሮ ውድነት ጋራ ተደምሮ በተለይ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ከኢኮኖሚና የተረጋጋ ማህበረሰብ ከመገንባት አንጻር አስተዋጽኦ ስላለው ልዩ ትኩረት ይሻል ማህበረሰቡ ላይ ምስቅልቅል እየፈጠረ ነው ሲሉ አቶ ቁምላቸው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በአከራዮች ላይ የተጣለው ከፍተኛ የታክስ መጠን፣ አከራዮች ይህንኑ ታክስ ወደ ተከራዩ እንዲያስተላልፉ እና ከውል ውጭ ተጨማሪ ክፍያ እንዲጠይቁ ምክንያት ሆኗል የሚሉት የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም ከመንግስት መፍትሄ ይፈልጋል ብለዋል።
ስለሆነም መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት የኑሮ ውድነቱን፣ የዋጋ ግሽበቱን፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሬውንና እጥረቱ በማዕቀፍ ለመፍታት እንዲያስችል ከዚህ በላይ የተቀናጀ ርብርብ እንዲያደርጉ ድርጅቱ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት የቤት ኪራይ ውድነትን ለመከላከል ይበጃሉ ያላቸውን መፍትሄዎች ማቅረቡንም ጠቅሷል፡፡
መንግስት በህገ-መንግስቱ በተደነገገው መሰረት አቅም በፈቀደ መጠን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው የማድረግ የፖሊሲ ዓላማና ኃላፊነት አለበት ያለው ድርጅቱ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በመሆኑ አቅርቦቱን ለማሟላት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በከተሞች ያለውን የቤት ኪራይ ዋጋ የማኅበረሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበና ተመጣጣኝ እንዲሆን የማድረግ፣ የመቆጣጠርና የማስተዳደር ሕጋዊ ግዴታን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡
ይህ አስፈላጊ ጣልቃ ገብነት የአከራዮችንና የተከራዮችን መሠረታዊ መብቶችና ጥቅሞች ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችል ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ለመዘርጋት ወሳኝ ነው ብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ ውሉ በመጪው ሰኔ 30/2018 ዓ.ም የሚያበቃ መሆኑን ተናግሮ ይህንን አስመልክቶም ጥናት እያስጠናሁ ነው ሲል ነግሮናል፡፡
በጥናቱ መሰረትም የኪራይ ዋጋ ባለበት እንደሚቀጥል፣ አሊያም ባለው የገበያ ዋጋ መሰረት የሚጨምር ወይም የሚቀንስ መሆኑን ለማህበረሰቡ አሳውቃለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7

