ለዓሣ እርባታ አመቺ የሚባል የውሃ አካል የሌላት አዲስ አበባ ዓሣ ማምረት ጀምራለች ተብሏል፡፡
- 2 hours ago
- 2 min read
ሐምሌ 1/2018
ለዓሣ እርባታ አመቺ የሚባል የውሃ አካል የሌላት አዲስ አበባ ዓሣ ማምረት ጀምራለች ተብሏል፡፡
ለመሆኑ የአዲስ አበባ የአየር ንብረት ዓሣ ለማምረት አመቺ ነው ወይ? አሁን እየተመረተ ያለው እንዴት ነው ስንል ጠይቀናል፡፡
ይህ ስራ የተጀመረው በከተማዋ የኮሪደር ልማት መሰራት ከተጀመረ ወዲህ እንደሆነ የነገረን የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በከተማዋ ዓሣ እየተመረተ ያለው አነስ ያሉ ሰው ሰራሽ ኩሬዎችን በማዘጋጀት ነው፤ በዚህ ዓመትም ከ23 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ዓሣ መመረቱን ጠቅሷል፡፡
በኮሚሽኑ የእስሳት እርባታ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቢኒያም አድማሱ ብዙዎች ባይረዱትም እንኳን አዲስ 43 ማህበራት በዚህ መንገድ እያመረቱ ነው፤ ለዚህ አካባቢ ተስማሚ የዓሣ ዝርያዎችም ቆሮሶ ወይም በባለሙያዎቹ አጠራር ቴላፒያና ካት ፊሽ የሚባሉት እንደሆነም ነግረውናል፡፡
በከተማዋ ዓሣን የመመገብ ፍላጎት እንዳለ እናስተውላለን፤ ከሌሎች ቦታዎች ከሚመጣ እዚሁ የሚመረትበት መንገድ ተመቻችቷል በ11ዱን ክፍለ ከተሞች የሰው ሰራሽ የዓሣ ኩሬዎች ተዘጋጅተዋል ብለውናል፡፡
በከተማዋ በተለይ የኮሪደር ልማቱ በተሰራባቸው አካባቢዎች የተባሉት ለዓሣ እርባታ ተብለው የተዘጋጁ አነስ አነስ ያሉ ቦታዎች ቢኖሩም እንደተመለከትነው በአንዳንዶቹ ውሃውም ዓሣውም የለም ያልናቸው ባለሙያው፤ ይህ የሚፈጠረው ከእውቀት ችግር ነው፤ ስለ እርባታው ስልጠና ብንሰጥም አንዳንዶች ለአዓ ምርት ኩሬ እንዲሆኑ የሚዘጋጁ ቦታዎችን በንጽህና ባለመያዝ፤ የሚፈለገው ዓይነት ውሃ ባለመሙላትና በሌሎችም ምክንያቶችነው ብለውናል፡፡
ለመሆኑ በሰው ሰራሽ መንገዶች ዓሣ መማምት ምን ያስፈልጋል?
ከባለሙያው ከአቶ ቢኒያም እንደሰማነው ዓሣን በዚህ መንገድ ለማምረት ለመጠጥ የሚሆነው ክሎሪን ያለበት ውሃ በፍፁም አይሆንም፤ ለምርቱ የግድ የጉድጓድ ወይም የከርሰ ምድር የሚባለው የውሃ ዓይነት መሆን አለበት፤ የዓሣ ጫጩትና መኖ የሚያቀርቡ ድርጅቶች አሉ፤ ለዚህም ማንኛውም ፍላጎቱ ያለው ሰው በቤቱ ለማምረት የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ማነጋገር ይቻላል ተብሏል፡፡
አሁን በከተማዋ እየተካሄደ ባለው የወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ አበባ ወንዞቿ ንፁህ ሲሆኑ ምን ያህል የማምረት አቅም ይኖራት ይሆን የሚለውን በዝርዝር የሚያስረዳ ጥናት በኮሚሽኑ ተከውኗ፤ በቅርቡ ጥናቱ ይፋ ተደርጎ ወደ ተግባር ሲገባ ዓሣ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንግዳ ነገር አይሆንም ብለውናል ባለሙያው፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ……
ምንታምር ፀጋው

