top of page

ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እየቀረበ ካለው መድሃኒት ከ40 በመቶ በላዩ በሃገር ቤት የተመረተ መሆኑ ተነገረ፡፡

  • sheger1021fm
  • 1 minute ago
  • 1 min read

ጥር 27/2018

 

ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እየቀረበ ካለው መድሃኒት ከ40 በመቶ በላዩ በሃገር ቤት የተመረተ መሆኑ ተነገረ፡፡

 

በ5 ዓመታት ጊዜ ውስጥም የፍጆታውን ከ1/3ኛ ወይም ከ60 በመቶ በላዩን  መድሃኒት በሃገር ቤት ማምረት እንደሚቻልም ከጤና ሚኒስቴር ሰምተናል፡፡

 

በኢትዮጵያ ለህክምና ግልጋሎት የሚውሉ መድሃኒቶችንና የህክምና ግብዓቶችን ከውጭ በማስገባት የሃገር ውስጡ ፍላጎት እንደሚሸፈን ይታወቃል፡፡

 

ለረጅም ዓመታት የሃገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾች ድርሻ ከ8 እስከ 10 በመቶ ሳይበልጥ እንደቆየ በጤና ሚኒስቴር የድንገተኛ ህክምና የመድሃኒቶችና ግብዓቶች አቅርቦት አማካሪ የሆኑት አቶ መሃመድ አማን ጀማል ነግረውናል፡፡

 

የመንግስቱን ጨምሮ በሃገር ውስጥ ያሉ 12 የግል የህክምና መሳሪያና መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች የኢትዮጵያን 40 በመቶ የመድሃኒት ፍላጎት እየሸፈኑ ነው፤ ምርቶቻቸውን እንዲያቀርቡም የተለየ የጨረታ እድል ተከፍቶላቸዋል ብለዋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ አምራቾቹ እስከ 7 ዓመት የሚደርስ የገበያ ዋስትና እንዲያገኙና ከቀረጥ ነፃ የሆኑ ማበረታቻዎች እንዲመቻቹላቸው በመደረጉ በተሻለ መንገድ እያመረቱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

 

የዛሬ 4 ዓመት ማስክና አልኮል ሳይቀር ከውጭ ይገባ እንደነበር የሚያስታውሱት የሚኒስቴሩ አማካሪ አቶ መሃመድ አማን፤ አሁን እንደ ሃገር በተፈጠረው አቅም ትልልቅ የህክምና ግብዓቶችም ጭምር በሃገር ቤት እየተመረቱ ነው፤ በመጪዎቹ 5 ዓመታትም ከ60 በመቶ በላይ የሃገር ውስጥ የመድሃኒት ፍላጎት በሃገር ውስጥ ምርት ይተካል ነው ያሉት፡፡

 

ለአምራቾች እየተሰጡ ያሉ ማበረታቻዎች ኢንቨስተሮችን ወደ ዘርፉ እየሳቡ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 

ከ5 ዓመታት በፊት ተከስቶ የነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከሳኒታይዘር ጀምሮ  እስከ መተንፈሻ መሳሪያዎች ድረስ ያሉብን ክፍተቶች አጉልቶ ያሳየን ነበር፡፡

 

ከዚህ በኋላ ነው፤ አምራቾቹን ለመደገፍ ምን እንስራ ብለን ተነስተን አብዛኛው ምርት የተመረተው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

 

የህብረተሰቡን ፍላጎት ተከትሎ የሕክምና ተቋማት እየተስፋፉ መምጣትና  የመድሃኒትና የህክምና ግብዓት ፍላጎት መጨመር ለመድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ገበያ ይሆናል መባሉንም ሰምተናል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…..

 

ምንታምር ፀጋው

 

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page