ህዳር 15 2018''ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ሀገር እንድትሆ የነበራትን ድርሻ ሀገሪቱን በማረጋገቱ ላይም ለራሷ ስትል ሀላፊነቷን ልትወጣ ይገባል'' ሲሉ በህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተናገሩ፡፡
- sheger1021fm
- Nov 25
- 2 min read

የአሜሪካ የተራዕዶ ድርጅት USAID የድጋፍ ፖሊሲውን መቀየሩ የኢትዮጵያን የስደተኛ ምላሽ ፈተና ውስጥ ከትቶታል ተብሏል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነጋዎ(ዶ/ር) ይህን የተናገሩት የስደተኞች እና ስደት ተመላሾች አገልግሎት ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር የ3 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው።
የተቋሙን ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በ27 መጠለያ ጣቢያዎች ወስጥ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።
95 ከመቶ ወይም ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉት ስደተኞች ከጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ መሆናቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተ፤ ከ41 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከደቡብ ሱዳን፣ 33 በመቶ ከሶማሊያ፣ 17 ከመቶ ከኤርትራ እና ከሌሎች ሀገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ጋምቤላ ክልል ያለው መጠለያ ከ 400,000 በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን በማስጠለል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ሲሆን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከ112,000 በላይ፣ አፋር ክልል ከ61,000 በላይ በመቀሌ እና በአዲስ አበባ በአጠቃላይ በከተሞች 70,000 ስደተኞች እንዳሉ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ 2ኛ ከአለም ደግሞ 7ኛው በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ እያኖረች ያለች ሀገር እንደሆነችም ተነግሯል፡፡
ባለፉት 3 ወራት ከ2,200 በላይ ስደተኞች እውቅና እንደተሰጣቸው ያስረዱት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን ከ21,600 በላይ ጥገኛ ጠያቂዎችን በደረጃ አንድ ከ5,440 በላይ ደግሞ በደረጃ ሁለት ተመዝግበዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
82 ስደተኞች ደግሞ የተለያዩ ህግወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ህጋዊ እውቅናቸው እንዲነሳ መደረጉን ወ/ሮ ጠቢባ አስረድተዋል፡፡
ከ164 የሚሆኑ ስደተኞችን ደግሞ ወደ ሶስተኛ ሀገር መላክ ተችሏል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የተራዕዶ ድርጅት USAID ድጋፉን በማቆሙ በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶች ስራቸውን እንዲቆሙ እና ሰራተኞቻቸውን እንዲበትኑ ማድረጉን የስደተኞች እና ስደት ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡
ከለጋሾች የሚቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ 40 በመቶ ወርዷል ተብሏል፡፡
ወ/ሮ ጠይባ የበጀት እጥረት፣ የጸጥታ ችግር፣ የሃይል አቅርቦት፣ ለስደተኞች የሚቀርብ ወራዊ የሬሽን ድጋፍ፣ ለትምህርት፣ ለጤና እና መሰል አገልግሎቶች የሚቀርብ ድጋፍ በእጅጉ መቀነሱን አግልግሎቱ የጋጠሙትን ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በድንብር አካባቢም ሆነ በክልሎች ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች ለስራቸውን እንቀፋት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
''እኛ የመንግስት ተቋም ስለሆንን መቀጠል ቻልን እንጂ ከUSAID እና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ የሚያገኙ ፤ በትምህር እና በጤና ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች መስሪያ ቤታቸውን ዝግተዋል፣ ሰራተኞቻቸውን በትነዋል፣ ስራዎቻቸውን አቋርጠዋል ያ ደግሞ በእኛ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል'' ብለዋል፡፡
የማጠቃለያ ሃሳበ የሰጡት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ መሆኑን ተናግረው ሀገሪቱ ካለት አቅም ጋር ሲነጻጸር ግን ከፍተኛ ሸክም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህን ሸክም ኢትዮጵያ ብቻዋን ልትወጣው ስለማትችል አለም አቀፍ ድርጅቶች ይህን መደገፍ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የጸጥታ የግጭት እና ጦርነት ችግር ያለባቸው እንደሆኑ የተናገሩት ዲማ ነጋዎ (ዶ/ር) የሚበዛው ስደተኛም ከጎረቤት ሀገራት የመጡ መሆናቸው ጠቁመዋል፡፡
ከጎረቤት አገራት ወስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ወይም ከአጠቃላይ 41 በመቶው የሚሆነው ደቡብ ሱዳናዊ መሆኑን ጠቁመው ደቡብ ሱዳን አገር ሆና እንድትፈጠር ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ብለዋል፡፡
የደቡብ ስዳን ስደተኞች ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ መኖራቸውን ተናግረው አሁን በሀገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን ያሉት ጭምር አዚህ በስደት ይኖሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡
አሁን በጋምቤላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደቡብ ሱዳናዊ ስደተኛ መኖሩን ያስታወሱት ዲማ ነጋዎ (ዶ/ር) ይህ የክልሉ ሁኔታ ሊያናጋ ስለሚችል ኢትዮጵያ ለራሷ ስትል በአገሪቱ ያለው ችግር የመፍታት እና ስደተኞችን ወደእዚያ መመለስ አለባት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments