top of page

የባህር ማዶ ወሬዎች - ሰኔ 5 2017

  • sheger1021fm
  • Jun 12
  • 2 min read

የሊባኖስ የቀድሞ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሚን ሰላም በምዝበራ ምክንያት ተይዘው ታሰሩ፡፡


አሚን ሰላም ተይዘው የታሰሩት በሀላፊነት ላይ እያሉ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተመደበን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ተብለው እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞው ሚኒስትር የግል ጥቅማቸውን መሰረት ያደረገ መንግስታዊ ኮንትራት ሰጥተዋል ተብለውም ተወንጅለዋል፡፡


አሚን ሰላም በዚሁ ጉዳይ ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል ተብሏል፡፡በምዝበራ እና በገንዘብ ማሸሽም ክስ እንደተመሰረተባቸው ታውቋል፡፡


ሊባኖስ ምስቅልቅሉ የየወጣውን ምጣኔ ሐብቷን ለማቃናት ደፋ ቀና ላይ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡

በኬንያ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ በእስር ቤት ሞቶ የተገኘው ወጣት መምህር አልበርት አጅዋንግ በፖሊሶች መገደሉን ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ አወገዙት፡፡


ኦጅዋንግ ከመምህርነቱ በተጨማሪ በድረ ገፆች ላይ ተነባቢ መጣጥፎችን በማውጣት እንደሚታወቅ አናዶሉ ፅፏል፡፡

ፖሊስ ግለሰቡ ህይወቱ ያለፈው ራሱን ከእስር ቤቱ ግድግዳ ጋር በማጋጨቱ ነው የሚል መግለጫ አውጥቶ እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


ሆኖም የወጣቱ ቤተሰቦች በሌሎች የአካሉ ክፍሎች ላይ የድብደባ ምልክቶችን አይተናል ብለዋል፡፡


በወጣቱ ላይ በእስር ቤት ውስጥ የተፈፀመው ግድያ በኬኒያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ እና ሐዘን ቀስቅሶ ሰንብቷል፡፡


ፕሬዘዳንቱ ለሟቹ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡


በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ምርመራ እና ማጣራት እንዲደረግም ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡

የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የፍልስጤም አስተዳደር ታላቅ ማሻሻያ ለማድረስ ስለመሰናዳቱ በቂ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ አሉ፡፡


ማክሮን ስለ ማሻሻያው ከአስተዳደሩ ሹሞች ቃል ተገብቶልኛል ማለታቸውን ሬውተርስ ፅፏል፡፡


የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት አስተያየት የተሰማው በመጪው ሳምንት የፍልስጤማውያንን የነፃ አገር ባለቤትነት የተመለከተ አለም አቀፍ ጉባኤ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው፡፡


ፈረንሳይም ለፍልስጤም ነፃ አገርነት እውቅና ለመስጠት መሰናዳቷ ሲነገር ሰንብቷል፡፡


በፍልስጤም ጉዳይ የሚመክረው አለም አቀፋዊ ጉባኤ የተሰናዳው በፈረንሳይ እና በሳውዲ አረቢያ ትብብር መሆኑ ታውቋል፡፡


ይሁንና በውጥኑ ሐማስ ከእንግዲህ ትጥቁን አስረክቦ በጋዛ ምንም ዓይነት ሚና አይኖረውም መባሉን ታጣቂ ቡድኑ እንዳጣጣለው ተሰምቷል፡፡


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

አሜሪካ በኢራቅ የሚገኙ የኤምባሲ ባልደረቦችን ብዛት እየቀነሰች ነው፡፡


እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት በስተቀር በባግዳድ የአሜሪካ ኤምባሲ ባልደረቦች ከነቤተሰቦቻቸው ለቅቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት በኢራቅ ባግዳድ የኤምባሲ ባልደረቦቸውን የሚቀንሱት በምን ምክንያት እንደሆነ በዝርዝር ያነሱት ነገር የለም፡፡


ምናልባትም አሜሪካ በኢራን ላይ ትወስደዋለች ከተባለ ወታደራዊ እርምጃ ጋር ተያያዥነት ሳይኖረው እንደማይቀር ተገምቷል፡፡


ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ኒኩሊየር ነክ ንግግራችን ወደ ስምምነት ሊያደርሰን አይችልም የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

ምናልባት በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ሁለቱ አገሮች ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ የሚለው ግምት አይሏል፡፡


የኢራን ሹሞች ቀደም ሲል አንዳች ጥቃት የሚሰነዘርብን ከሆነ በቀጠናው ባሉ የአሜሪካ ተቋማት ላይ ምላሻችን የከፋ ይሆናል ሲሉ መዛታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page