‘’በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ጃዊ ቀበሌና በሮቤ ወረዳ ገባ ቀበሌ በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልተለዩ ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጫለሁ ’’
- Mar 4
- 2 min read
የካቲት 25/2018
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በዞኑ ሽርካ ወረዳ ጃዊ ቀበሌ እና በሮቤ ወረዳ ገባ ቀበሌ በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልተለዩ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አረጋግጫለሁ አለ፡፡
የሕይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ፣ አካል ጉዳት፣ እገታ እንዲሁም መፈናቀል የደረሰባቸው ሰዎች አንዳሉ በተለያዩ መንገዶች ባሰባሰብኳቸው መረጃዎች አረጋግጫለሁ ብሏል።
ጥቅቱንም የፈጸመው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) መሆኑን ኮሚሽኑ ባወጣው መገልጫ አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በአርሲ በተለያዩ ወረዳዎች በአዲስ መልክ በቀጠለው ጥቃት የ21 ንጹሐን ህይወት ማለፉን መናገሩ ይታወሳል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች የሚፈጸመው ጥቃት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እያስከተለ ነው ብለዋል፡፡

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት የሆኑት በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ጉዳቶች፣ ማፈናቀሎች፣ እገታዎች እንዲሁም የንብረት ውድመቶችና ዘረፋዎች የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ጨምሮ ነዋሪዎች በሰላምና በደህንነት የዕለት ተዕለት ተግባራትን እንዳያከናውኑ አስቸጋሪ አድርጎታል ማለታቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል።
ዋና ኮሚሽነሩ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥታት በተደጋጋሚ ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው እና የጥቃት ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች በቂ የጸጥታ አካላትን እንዲያሰማሩ እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲያመቻቹ እንዲሁም ተመሳሳይ ጥቃቶችን ቀድሞ የመተንበይና የመከላከል ሥራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ያለው ሁኔታ ለተወሰኑ ጊዜያት እየተሻሻለ የነበረ ቢመስልም ከጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ኦነግ ሸኔ በሽርካ፣ በጉና፣ በመርቲ፣ በአሰኮ እና በኦንቆሌ ዋቤ ወረዳዎች በሰዎች ላይ በፈጸማቸው ጥቃቶች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ ጠቅሷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የደህንነት ሥጋቶች ምክንያት የነዋሪዎች መፈናቀል መከሰቱን ኢሰመኮ የደረሱትን ጥቆማዎችና አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ነዋሪዎችን እና የየአካባቢዎቹን የመንግሥት ኃላፊዎች በማነጋገር ባሰባሰባቸው መረጃዎች ማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል።
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments