ሰኔ 9 2017 - የተሽከርካሪ ጥሩንምባ በሚረብሻት ከተማ መስማት የተሳናቸው ያለችግር ማሽከርከር የሚችሉት እንዴት ነው?
- sheger1021fm
- Jun 16
- 2 min read
መስማት ለተሳናቸው የአሽከርካሪነት የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው፣ ማሽከርከርም እንዲፈቀድላቸው ለዓመታት ሲጠየቅ ቆይቷል::
ከ5 ዓመት በፊት የወጣው መመሪያ አሁን ፀድቆ መስማት የተሳናቸው የአሽከርካሪነት መንጃ ፈቃድ እንዲያወጡ ለማድረግ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡
ለመሆኑ መመሪያው ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት ምን ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የተሽከርካሪ ጥሩንምባ በሚረብሻት ከተማ ፣ አሽከርካሪዎች በክላክስ መረጃ መለዋወጣቸው ልማድ በሆነበት ጎዳና መስማት የተሳናቸው ያለችግር ማሽከርከር የሚችሉት እንዴት ነው?
ይህ በብዙ መልኩ መስማት የተሳናቸው ለሚያነሱት ጥያቄ መልካም ቢሆንም ወደ ተግባር ሲገባ ግን ምን ያህል ዝግጅት ተደርጎበታል በተለይ ከአደጋና የጥንቃቄ ስራዎችን ጋር በተያያዘ ያለው ሂደት ምን መሳይ መሆን አለበት ስንል የሚመለከታቸውን ጠይቀናል፡፡
ኢንጂነር ደሳለኝ ተረፈ የአዲስ አበባ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና አስኪያጅ ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት መመሪያው ወጥቶ ረጅም ዓመታት ማስቆጠሩንና በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የነበረ መሆኑን በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያም እስካሁን ወደ ተግባር አለመግባቱን ነግረውናል፡፡

የተለየያዩ ውይይቶችን ካደረግን በኋላ ዓለም አቀፍ ሂደቶችን ለመያዝ በመሞከር ጥናቶችን አስጠንተናል፤ ከአፍሪካ ሀገራትመስማት ለተሳናቸው የማሽከርከር ፈቃድ ያልሰጡ ስምንት ሀገራት ብቻ ናቸው ከስምንቱ ውስጥም ኢትዮጵያ አንዷ ነች ብለዋል፡፡
አለም አቀፍ ደረጃ በጣም በርካታ ሀገራት ይህንን ፈቃድ አሁን እያደረግን ያለነው የመጀመሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
የሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ጉዳይ ብዙ ጥንቃቄ የሚፈልግና በማሽከርከሩ ወቅት ሊደርስ የሚችል አደጋ ለመቀነስ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ሌሎችም አአለማቀፍ ልምዶች ምን ያህል ተወስዷል ስንል የጠየቅናቸው ኢንጂነር ደሳለኝ ጥናቱን ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ውጭ ሀገር የነበሩበትን ልምዳቸውን በማካፈል ወደዚህ ሲመጣ መሟላት ያለባቸውንና መደረግ የሚገባቸውን ቅድመ ጥያቄዎችን በሙሉ ያሟላ እንዲሆን የተካተተበት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚያሽረክሯቸው መኪኖች ከጎን ጀርባና እና ከፊት ለፊት ላይ ምልክት እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል፡፡
መመሪያው ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ ብዙ ጥያቄዎችን የሚመልስ መሆኑንና መስማት የተሳናቸው በሚያሽከረክሩበት ጊዜ የመንገድ ላይ አደጋዎችን በተቻለ መጠን ለመቀነስም በሌላ ሀገራት በስራ ላይ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚገጥማቸውንም ችግር ለመቀነስ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ዴቨሎፕመንት ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ጌታሁን ስምዖን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ መስማት የተሳናቸው ሰዎች መኖራቸውንና ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑት መመሪያው ከተረቀቀበት ከአምስት አመታት በፊት ጀምሮ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ተናግሯል፡፡
ስራው ወደ ተግባር መግባቱ የብዙዎችን ጥያቄ የሚመልስ በመሆኑም ከወዲሁ ለትራፊክ ፖሊሶች ለማስተዋወቅ ምክክር ማድረጉንም ማህበሩ ጠቅሷል፡፡
መስማት ለተሳናቸው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ስልጠናውን ለመስጠት አሁን ላይ ብቸኛው ማሰልጠኛ ኪባይ ኪ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ በዝግጅት ላይ ነው ተብሏል፤ ነገር ግን በመመሪያው የተፈቀደው ለግል አውቶ ሞቢል ስልጠና ብቻ ሲሆን የህዝብ ትራንስፖርትና የጭነት ተሽከርካሪዎች ስልጠና አለመካተቱን ሰምተናል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
ความคิดเห็น