top of page

ሰኔ 3 2017 - የ2018 የፌዴራል መንግስት አጠቃላይ በጀት የተገደበ የበጀት ጉድለት እንዲኖረው ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ተባለ።

  • sheger1021fm
  • Jun 10
  • 2 min read

ለዓመቱ የተዘጋጀው በጀት የ417 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ጉድለት ያለው እንደሆነ ተጠቅሷል።

ጉድለቱን ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ በሚገኝ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በ2018 ረቂቅ በጀት ዙሪያ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በማብራሪያቸው የ2018 የፌዴራል መንግስት ጠቅላላ ወጪ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊየን ብር ወይም 1 ትሪሊየን 928 ቢሊየን ብር እንዲሆን መቅረቡን ተናግረዋል

ገንዘቡ ለ2017 ተጨማሪ በጀትን ጨምሮ ፀድቆ ከነበረው የፌዴራል መንግስት የወጪ በጀት የብር 494 ቢሊየን ብር ወይም የ34 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነ ጠቅሰዋል

ከተያዘው አጠቃላይ በጀት 1 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ ፤ 415 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለካፒታል ወጪ ፤

 315 ቢሊየን ብር ለክልሎች የበጀት ድጋፍ እና 14 ቢሊየን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የተደለደለ መሆኑን ሚኒሰትሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል።

ከአጠቃላይ በጀቱ 61 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ ድርሻ ለመደበኛ በጀት የተያዘ ነው ያሉት  ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ፤ለ2017 ተመድቦ ከነበረው መደበኛ በጀት የ48 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።

 

ከተመደበው የፌዴራል መንግስት የመደበኛ ወጪ በጀት 39 ከፍተኛው ድርሻ የተደለደለው የማዕከላዊ መንግስትን የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዕዳ ለመክፈል ነው ብለዋል።

ለዓመቱ ከተመደበው የካፒታል በጀት ደግሞ ከ74 ነጥብ 5 በመቶ በላዩ ለዋና እና አገናኝ መንገዶች ግንባታ ፤

እንዲሁም ነባሮቹን ለማጠናከር ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እና ለመሰል መሰረት ልማቶች የተያዘ ነው ተብሏል ።

ለአመቱ ከተያዘው 1 ነጥብ 93 ትሪሊየን ብር ውስጥ 1 ነጥብ 23 ትሪሊየን ብር ታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ይህም የአጠቃላይ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዕርዳታ ገቢውን 81 በመቶ ይሸፍናል ነው ያሉት።

ቀሪው 19 በመቶ በጀት ከውጪ ዕርዳታ ይገኛል ተብሎ መታቀዱን ጠቅሰዋል።

የ2018 ረቂቅ በጀት ሲዘጋጅ ታሳቢ የተደረጉ የተለያዩ ጉዳዮች እንዳሉም ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል።

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት የ2018 የፌዴራል መንግስት አጠቃላይ በጀት የ417 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ጉድለት አለው ።

ይህን ጉድለት ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ በሚገኝ ብድር ለመሸፈን መታቀዱንም ተናግረዋል።

መንግስት ለዓመቱ የተያዘው በጀት በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን በጥብቅ እንደሚከታተልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ንጋቱ ረጋሣ

コメント


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page