'’የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ምክንያታዊ የሆነ የወንጀል ጥርጣሬ የሌለበት ሰው ስለ ንብረቱ እንዲያስረዳ አያስገድድም’’ የፍትህ ሚኒስቴር
የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ውጪ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ንብረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር ሳይሆን በአገር ውስጥ ሆነው የአገርንና የህዝብን ገንዘብ በሚዘርፉት ላይ ያነጣጠረ ሲሉ የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
አከራካሪና አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ፣ በ10 ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሶ፣ የንብረት ባለቤትነትን የሚያጣራ በመሆኑ በዜጎች ንብረት ላይ አሉታዊ አሰራር ይከተላል የሚል ብዥታ ፈጥሮ ረቂቅ አዋጁ በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር ቤት ልከው ያፈሩትን ሀብት ንብረት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚልና ሌሎችም አስተያየቶች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ረቂቅ አዋጁ ባለፉት 10 ዓመታት ያገኘውን ንብረት እንዲያስረዳ የሚጠይቅ አይደለም፡፡
ማንኛውም ሰው ስለ ንብረቱ እንዲያስረዳ የሚጠየቀው ከግምት ያለፈ ተጨባጭ የሆነ፣ ምክንያታዊ የወንጀል ጥርጣሬ ሲገኝበት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ፣ምክንያታዊ በሆነ በወንጀል የሚጠረጠር ሰው ክስ የሚቀርብበት በፍ/ብሔር ክስ እንደሚሆንና ነገር ግን ለመንግስት፣ ለህዝባዊ ድርጅቶች ሀላፊዎችና ሰራተኞች ግን በተጠያቂነት በወንጀል ክስ እንዲከሰሱ ነባሩ ህግ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ልከው ባፈሩት ንብረት ላይ አደጋ የሚጋርጥ ነው ተብሎ ስለሚነገረው ፍትህ ሚኒስትሩ “አይደለም” ብለዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት የረቂቅ አዋጁ ዓላማም በአገር ውስጥ ሆነው ህገወጥ በሆነ መንገድ በሙስና፣ በታክስ ስወራ፣ በሰው ንግድ፣ በእፅና በጦር መሳሪያ ዝውውር ተሰማርተው በህገወጥ መንገድ ንብረት ያፈሩትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ነው፡፡
ከውጪ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ቢሆንም በህጋዊ መንገድ ያገኙት እንደሆነ ታሳቢ በማድረግ ረቂቅ አዋጁ ረቂቅ አዋጁ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር አይደለም፡፡
በውጪ አገር እየኖሩ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት፣ ባፈሩት ንብረት ላይ ረቂቅ አዋጁ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ከተደረገው ጥንቃቄ በላይ፣ በአዋጁ ማፅደቁ ሒደትም ላይ ጥንቃቄ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ስለ ገንዘብ ምንዛሬና ደረሰኝ እንደማያነሳ ያስታወሱት ዶ/ር ጌዲዮን ግን ግን በህገወጥ የተፈራውን ንብረት “ከውጪ አገር የተላከልኝ ነው” በሚል ከለላ ለማድረግ የሚፈልጉትን እንደሚቆጣጠር ይጠቅሳሉ፡፡
የፍትህ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ በተጨማሪ የ10 ሚሊዮን የንብረት ግምት ገደብ የተደረገበትን፣ በውጪ አገር ስለሚቀመጡ የወንጀል ተጠርጣሪ ንብረቶችን ስለማስመለስ ከህገመንግስቱ ጋር ተጣጥሞና ስለመረቀቁና ፣ የፍርድ ቤቶችን ስልጣን እንደማይጋፋ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
留言