top of page

ጳጉሜ 3 2017 - በተለምዶ ሿሿ ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦች

  • sheger1021fm
  • 21 hours ago
  • 2 min read

በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት ከማታለል ጋር የተያያዙ በተለይም በትራንስፖርት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ወይም በተለምዶው #ሿሿ ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸው ይነገራል፤ ድርጊቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ የሚሰማ መሆኑ የማታለል ወንጀሉን የሚፈጸሙ ግለሰቦችም የሚጠቀሙት መንገድ ተመሳሳይ መሆኑ ቢነገርም ወንጀሉ ተደጋግሞ መሰማቱ ከጥንቃቄ ጉድለት ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡


ስለ ጉዳዩ የጠየቅነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በበኩሉ በየጊዜው ስለ ወንጀል ድርጊቶቹ አፈፃፀም ዝርዝር መረጃ እየሰጠን ግለሰቦችም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ቢነገርም የሚተገበሩት ግን ጥቂቶች ናቸው ብሏል፡፡


የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እንደነገሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ በየጊዜው በሚደርሰው ጥቆማ እንዲሁም በሚያደርገው ድንገተኛ ፍተሻ ተጠርጣሪዎቹን እንደሚያገኝና ክስ እየመሰረተ ለፍርድ ቤት እያቀረበ ነው ብለዋል፡፡

ree

ከሚመጡ ጥቆማዎች በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ አልፎ አልፎ በምናደርጋቸው ፍተሻዎች ወንጀል ፈጻሚዎችን እናገኛለን የሚሉት ኮማንደሩ ሌሎችም አካባቢዎች ላይ እንደዚህ አይነት ጠንካራ የሆነ የቁጥጥር ስራ እየሰራን ነው ወንጀል ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር ካዋልን በኋላ የምናገኛቸውን ንብረቶችም ህብረተሰቡ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ሄዶ እንዲወስድ እያደረግን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ነገር ግን ወንጀሎቹ በተደጋጋሚ ጊዜ መሰማታቸው የማጭበርበር መንገዶቹም ተመሳሳይ ቢሆንም አሁንም ይታያሉና ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ ላይ ምን እየተሰራ ነው ያልናቸው ኮማንደር ማርቆስ ህብረተሰቡ ብዙ ጊዜ የሚነገሩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን አለመተግበሩ ዋናው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡


በተለያዩ ሚድያዎች ላይ የሚተላለፉ የፖሊስ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ወደ ተግባር ካለመቀየር የሚመጡ እና ብዙዎቹ ተመሳሳይነት ያላቸው ወንጀሎች ናቸው ለዚህም በፖሊስ የሚነገሩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን አለመተግበር አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል ኮማንደር ማርቆስ፡፡


ግለሰቦች ወንጀል ሲፈጸምባቸው ለፖሊስ ጥቆማ የመስጠት ልምዱ ጨምሯል ወይ በዚህ አይነት ወንጀል ተጠርጥረው የሚመጡ ተከሳሾች ድግግሞሽ ምን ይመስላል ይህንንስ ለይታችኋል ወይ ስንል የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ካለፉት አመታት አንጻር በጣም ጥሩ የሆኑ መረጃዎች ወደ ፖሊስ እየመጡ ነው እነዚህን መረጃዎች በማጠናቀር እና ወደ ተግባራዊነት በመቀየር ወንጀል መከላከሉ ላይ በብርቱ እየሰራን ነው ይህንንም ጠንካራ የቁጥጥር ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡


በተደጋጋሚ ጊዜ በከተማዋ ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ወንጀሎችን ለመከላከል በብርቱ እየሰራሁ ነው ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ተይዘው ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚሰጠው የፍርድ ቅጣት አስተማሪ እንዲሆንም እንጠይቃለን ይህም ወንጀሎቹ ተደጋግሞ እንዳይከሰቱ እና ለማስተማርም የሚያግዝ ነው ብሏል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..


ምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page