top of page

ጥር 1፣2016 - አሽከርካሪዎችን በመግደል ተሽከርካሪዎችን ይዘው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ተናገረ

አሽከርካሪዎችን በመግደል ተሽከርካሪዎችን ይዘው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ተናገረ፡፡


በወንጀሉ የተወሰዱ ሁለት ተሽከርካሪዎችንም ማስመለስ ተችሏል ተብሏል፡፡


አቶ አብይ ክንፈ የተባሉ ግለሰብ ህዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ ከተማ ሰዎችን ለማድረስ በኮንትራት ተስማምተው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- B36969 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪያቸውን እየነዱ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው እንቁላል ፋብሪካ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተነስተው መጓዛቸውን ፖሊስ አስረድቷል፡፡

ይሁን እንጂ አቶ አብይ ከሄዱበት ሳይመለሱ መቅረታቸወን ፖሊስ ከቤተሰቦቻቸው መረጃ ድረሶታል፡፡

በተመሳሳይ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም አቶ ዲልፈታ ደንሰቦ የተባሉ ግለሰብ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B 21688 አ.አ የሆነ መኪና እያሽከረከሩ ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ ሰዎችን ለማድረስ ከሄዱበት ሳይመልሱ መቅረታቸው ለፖሊስ ሪፖርት ይደረጋል፡፡


አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ የሁለቱ ግለሰቦች መሰወርና የተሽከርካሪዎቹ ደብዛ መጥፋትን ፖሊስ ጠቅሷል፡፡


የአዲስ አበባ ፖሊስ በደረገው ክትትል የአቶ አብይ ክንፈ አስክሬን ሞጆ ከተማ እንዲሁም የአቶ ዲልፈታ ደንሰቦ አስክሬን ደግሞ ከሞጀ ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ተጥሎ መገኘቱን አረጋግጧል፡፡

ሁለቱም ግለሰቦች የተለያየ የሰውነት ክፍላቸው ላይ በስለት ተወግተው መሞታቸው እና ወንጀሉ የተፈፀመው በተመሳሳይ ቡድን ወይም ግለሰብ መሆኑንን ፖሊስ አስረድቷል፡፡


በሁለቱም ወንጀሎች ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ አራት ተጠርጣሪዎችን እና በመሸሸግ ወንጀል የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ መያዙንም ፖሊስ ይፋ አድርጓል ፡፡


ወንጀል ፈፃሚዎቹ ትራንስፖርት ፈላጊ መስለው በመቅረብ ሁለቱንም አሽከርካሪዎች በስለት በመውጋት እንደገደሏቸው በምርመራ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡


ተጠርጣዎቹ አሽከርካሪዎቹን ከገደሉ በኋላ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- B 21688 አዲስ አበባ የሆነውን ተሽከርካሪ ወደ ወላይታ ሶዶ በመውሰድ በአንደኛው ተጠርጣሪ ወላጆች መኖሪያ ግቢ ደብቀውት ተገኝቷል፡፡


ወንጀል የተፈፀመበት መኪና በግቢያቸው የተገኘው የተጠርጣሪው ቤተሰቦች ተሽከርካሪው ውስጥ የፈሰሰውን የሟች ደም በማጠብ ማስረጃ እንዳጠፉ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡


በተመሳሳይ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B 36969 አ.አ የሆነው ተሽከርካሪ ደግሞ ለአንድ ግለሰብ ተሽጦ ፖሊስ ባደረገው ብርቱ ክትትል ወላይታ አካባቢ ሊገኝ ችሏል፡፡


የአዲስ አበባ ፖሊስ የክትትል ቡድን አባላት ከአዲስ አበባ ሞጆ፣ ከሞጆ ሀዋሳ፣ ከሀዋሳ ሺንሽቾ እየተመላለሱ ጎዳና ተዳዳሪ መስለው መረጃ እና ማስረጃ ለማሰባሰብ ለበርካታ ቀናት ጎዳና ላይ በማደር ተጠርጣዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ተብሏል፡፡




#በተጨማሪም የተለያዩ ሀሰተኞች ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበበ ፖሊስ ኮሚሽን ተናገረ።


ፖሊስ ሀሰተኛ ሰነድ በሚያዘጋጁ ግለሰቦች ላይ ባደረገው ክትትል ልዩ ልዩ ሀሰተኛ ሠነዶችንና ሰነዶቹን ለማዘጋጀት የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሏል ተብሏል።


ፖሊስ አብነት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሀሰተኛ ሰነድ በሚዘጋጅበት መኖሪያ ቤት ውስጥ በህግ አግባብ ባደረገው ብርበራ 13 ሀሰተኛ የመኪና ሊብሬ፣ 10 ሀሰተኛ የቤት ካርታ፣ 2 ሀሰተኛ የጋብቻ ሰርተፍኬት፣ 18 የእጅ በእጅ የሽያጭ ደረሰኞች፣ 6 ሀሰተኛ የባንክ ቤት ደረሰኞች መያዛቸው ተነግሯል።


የተለያዩ የዲግሪ፣ የዲፕሎማ እና የስምንተኛ ክፍል የትምህርት ማስረጃዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ሀሰተኛ የስራ ልምድ እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት ሀሰተኛ አርማዎች (ሎጎ) መገኘታቸውንም የጌጃ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊ ኮማንደር በልሁ ክፍሌ ተናግረዋል።


ተጠርጣሪዎቹ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ፖሊስ አስረድቷል።



ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



bottom of page