ግንቦት 26 2017 - ከስርዓተ ምግብ ጋር ተያይዘው የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ውጤታማነታቸው እንዲታይ ቀጥታ ማህበረሰብ ላይ ወርደው መስራት አለባቸው ተባለ
- sheger1021fm
- Jun 3
- 2 min read
ከስርዓተ ምግብ ጋር ተያይዘው በኢትዮጵያ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ዘላቂ እንዲሆኑና ውጤታማነታቸው እንዲታይ ከጥናትና የወረቀት ስራዎች ይልቅ ቀጥታ ማህበረሰብ ላይ ወርደው መስራት አለባቸው ተባለ፡፡
ምንም እንኳን በተለያየ ጊዜ ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተገናኘ በርካታ ፕሮጀክቶች ቢቀረጹም የታለመላቸውን ሳያሳኩ የሚቋረጡ አሉ ተብሏል፡፡
ለዚህም ስራዎቹ ቀጥታ ማህበረሰብን የሚያካተቱ ሆነው መተግበር ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል ሲሉ የነገሩን በኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ላይ የሚሠራው ዘ ሀንገር ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተሾመ ሽብሩ ናቸው፡፡
አብዛኛዎቹ ኒውትሪሽን ላይ የሚቀረጹ ፕሮጀክቶች ዘላቂነት የሚያጡት ህብረተሰቡ በሚገባ ባለቤት ወይም መሪ ሆኖ ስለማይከናወኑ ነው፤ በአብዛኛው ፕሮጀክቶች የሚወድቁት ህብረተሰቡ በሚገባ ግንዛቤ ፈጥሮ ከዛ በኋላ እኛ ባለሙያ ነን ብለን እዛ የምንሄደው ሳንሆን ራሱ መናገር ሲጀምር ነው ብለዋል፡፡
ቀጥታ ማህበረሰብን በጉዳዩ ላይ በማሳተፍ የሚሰሩ ስራዎች ውጤት ይኖራቸዋል የሚሉት አቶ ተሾመ በተለይ ምግብ አምራች በሆኑ አርሶ አደሮች ላይ ቀጥታ መስራት የተሰባጠረ የምግብ ምርት እንዲኖር በማድረግ ሌሎችንም የሚጠቀም ማድረግ ቢቻልም በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ግን በተቃራኒ ነው ይላሉ፡፡

የግብርና የአመራረት ሥርዓታችን ስፔሻላይዝ እያረግን ገበያ ተኮር እየሆነ መምጣቱ አንድ ዓይነት ምርቶች ብቻ መወሰኑ የተለያየ የምርት አለመኖሩ አማራጭ እና የተለያየ የምግብ ስብጥር እንዳይኖር የሚያደርግ ነው ሲሉ አቶ ተሾመ ተናግረዋል፡፡
የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ ከጤና በተጨማሪ በትውልድ ላይ የሚሰራበት ቢሆንም የሚያደርሰው ጉዳትም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያርፍ ነው ለዚህም በግል ድርጅቶችም ይሁን በመንግስት የሚቀረፁ የዘርፉ ፖሊሲዎች ከሐሳብ ባለፈ በተግባር የሚታዩ መሆን አለባቸው ሲሉ አቶ ተሾመ ነግረውናል፡፡
በኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ ላይ በመንግስት እንዲሁም የለጋሾች ድርጅቶችን ጨምሮ የሚሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰት መቀንጨር ግን ከነበረበት 37 በመቶ ጨምሮ በቅርብ በወጣ ሪፖርት ወደ 39 በመቶ ማሻቀቡ ተነግሯል፡፡
ለዚህም የምግብ ዋጋ መናር፣ ጦርነትና ድርቅ ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል፤ ለመፍትሄውም ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተጣጥሞ የሚሄድና ውጤታማነቱ የተመዘነ ቀጥታ በማህበረሰብ ላይ የሚተገበር የስርዓተ ምግብ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ተመክሯል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il












Comments