የዲዛይን ችግር፣ የፀጥታ መደፍረስና የወሰን ማስከበር ላይ በሚያጋጥሙ ፈተናዎች እና የበጀት እጥረት ዘጠኝ ያህል የመስኖ ፕሮጀክቶች መስተጓጎላቸው ተነገረ፡፡
- Apr 23
- 2 min read
ሚያዝያ 15/2018
የዲዛይን ችግር፣ የፀጥታ መደፍረስና የወሰን ማስከበር ላይ በሚያጋጥሙ ፈተናዎች እና የበጀት እጥረት ዘጠኝ ያህል የመስኖ ፕሮጀክቶች መስተጓጎላቸው ተነገረ፡፡
የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር እንዳለው ከተጠቀሱት ችግሮች ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የነዳጅ አቅርቦት ችግርም ለመስኖ ፕሮጀክቶች ፈተና ሆኗል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወራት የስራ ክንውን ሪፖርት እንደሚያሳየው የዲዛይን ስራቸው ሳይጠናቀቅ የተጀመሩ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ስራ መጀመር ካለባቸው ጊዜ የመዘግየት ችግር አጋጥሟቸዋል፡፡
ከመካከላቸው የሎግያ ፣ ፈንታሌ ፣ ሽንሌና አንገር የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥልቅ ጥናት ባልተደረገባቸው ዲዛይኖች የተጀመሩ ናቸው ተብሏል፡፡
በመሆኑም በአማካሪ ድርጅቶች የዲዛይን ማስተካከያ ተደርጎላቸው ወደ ስራ እስኪመለሱ የመዘግየት ችግር ያጋጠማቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ከሪፖርቱ ተመልክተናል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግርም ለመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መዘግየት ሌላው ፈተና ሆኖ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ቀደም በዲዛይን ችግርና መሬት በመንሸራተቱ ለአመታት መዘግየቱ ሲነገር የቆየው የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት አሁን ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት የመዘግየት ችግር ካጋጠማቸው መካከል ሆኖ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም የላይኛው ርብ የመስኖ ፕሮጀክት በፀጥታ ችግር ምክንያት ሙሉ በሙለ ስራው መቆሙ ተሰምቷል፡፡
በሌላ በኩል የመስኖ ፕሮጀክቶች በባህሪያቸው ውስብስብ በመሆናቸው ከፍተኛ የማስፈፀሚያ ሀብት እንደሚያስፈልጋቸው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በሪፖርቱ አስታውሷል፡፡
ይሁንና የሀገር አቅም በፈቀደ መጠን በጀት ካልተመደበ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ሊጠናቀቁ አይችሉም ይህም ተጨማሪ በጀት እንዲጠይቁ ሊያስገድድ ይችላል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
አብዛኛው የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በአርሶ አደሮች ይዞታ ላይ በመሆኑ እየቀረቡ ያሉ የካሣ ክፍያ ጥያቄዎች በፍርድ ቤት የሚኒስቴር መ/ቤቱን የባንክ ሂሳብ እስከ ማሳገድ ደርሰዋል ተብሏል፡፡
የወሰን ማስከበር ጉዳይን እልባት ይሰጣል የተባለና ክልሎች በየአካባቢያቸው የሚፈፀም ፕሮጀክት ለወሰን ማስከበር ካሣ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ አዋጅ ቢፀድቅም ክልሎች በሚጠበቅባቸው ልክ ወደ ተግባር አልገቡም ብሏል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በሪፖርቱ፡፡
እንዲሁም በቀድሞው የካሳ አዋጅ መሰረት አንዳንድ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት በመውድም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተቋሙ ክፍያ ከመፈፀም ባለፈ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የባንክ ሂሳብ እስከ ማገድም ደርሷል ተብሏል፡፡
የተጠቀሱት በተለያዩ የመስኖ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትም ሚኒስቴሩ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን በሪፖርቱ አካቷል፡፡
የፀጥታ ችግሩ መስተጓጎል የፈጠረባቸውን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የስራ ሀላፊዎች ጋር በመነጋገርና በጋራ በመስራት በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ እንዳይወቆሙ ጥረት አድርጊያለሁ ብሏል፡፡
የዲዛይን ችግር ያለባቸውንም በመለየት፣ አማካሪ ድርጅቶች በፍጥነት የዲዛይን ክለሳ አድርገው እንዲያጠናቅቁ ጥብቅ ክትትል እያደረግሁ ነው ያለው ሚኒስቴሩ ፕሮጀክቶች እንዲዘገዩ እያደረጉ ላሉ ሌሎች ችግሮችም መላ እየፈለግሁ ነው ብሏል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments